Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን የተባለ ግለሰብን በማገት መኪና ለመንጠቅ ሊብሬውን በመቀየር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን የተባለ ግለሰብን በማገት መኪና ለመንጠቅ ሊብሬውን በመቀየር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ።

የክስ መመስረቻ የ15 ቀን ጊዜ ለዐቃቤ ሕግ የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

ተጠርጣሪዎቹ÷ 1ኛ የኡስታዝ አቡበከር ሁሴንን ተሽከርካሪ በስሙ አዙሯል የተባለው አበራ ነጋሳ፣ 2ኛ ተጠርጣሪ ደግሞ የ1ኛ ተጠርጣሪ ወኪል በመሆን የተሽከርካሪውን ባለቤት ስም ወደ አንደኛ ተጠርጣሪ አዙሯል የተባለው ፍፁም ተክለ አብረሃ እና 3ኛ በአዲስ አበባ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አዲስ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሲስተም ሰራተኛ ሆኖ ሲሰራ በኡስታዝ አቡበከር ስም የተመዘገበውን ተሽከርካሪ በአንደኛ ተጠርጣሪ ስም ሲስተም ላይ ቀይሯል የተባለው አቶ ተከታይ ዘገየ እንዲሁም በዚሁ ተቋም ሰራተኛ የሆነውና ኡስታዝ አቡበከር የቦሎ እድሳትን በተሽከርካሪው ታርጋ ቁጥር በ1ኛ ተጠርጣሪ ስም በመቀየር ቦሎ እንደታደሰ አድርጎ ቀይሯል ተብሎ የተጠረጠረው አብዮት አበራ ናቸው።

ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ጋር በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠረና በሌላ መዝገብ በጊዜ ቀጠሮ ችሎት እየታየ የሚገኘው ሌላኛው የኡስታዝ አቡበከር የመኪና ሊብሬን በ1ኛ ተጠርጣሪ ስም ቀይሯል የተባለው የአዲስ አበባ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አዲስ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሰራተኛ የሆነው ልየው አሰፋ ይገኛል።

ባጠቃላይ እነዚህና ሌሎች ከ3 ተቋማት የተውጣጡ 9 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች በመመሳጠርና በመደራጀት ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን የተባለ ግለሰብን በማገት የተሽከርካሪውን ሊብሬ በሌላ ሰው ስም በመቀየር፣ ቦሎም በተቀየረ ሰው ስም እንዲታደስ በማድረግ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ናቸው።
የተለያዩ የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት በጋራ ክትትል ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ከመስከረም 9 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የጊዜ ቀጠሮ ምርመራ ስራውን ሲያከናውን የቆየው የአዲስ አበባ ፖሊስ መርማሪ በተለይም በአራቱ ተጠርጣሪዎች ላይ የምርመራ ስራውን አጠናቆ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ማስረከቡን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስረድቷል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በችሎት ተገኝቶ የምርመራ መዝገቡን ዛሬ ጠዋት ከፖሊስ መረከቡን በመግለጽ መዝገቡን ተመልክቶ ክስ ለመመስረት እንዲያስችለው 15 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ ጠይቋል።

የ1ኛ እና የ2ኛ ተጠርጣሪ ጠበቆች ደንበኞቻቸው ላይ በፖሊስ ምርመራ ሲደረግ ዐቃቤ ሕግ ምርመራውን ሲመራ እንደቆየ ጠቅሰው እንደ አዲስ መዝገቡን ተመልክቶ ክስ ለመመስረት 15 ቀናት ይሰጠኝ ማለቱ አግባብ አይደለም በማለት ጥያቄውን በመቃወም ተከራክረዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ጋር በተመሳሳይ ወንጀል ምርመራ እየተደረገባቸው ያሉ ሌሎች ግብረ- አበሮች መኖራቸውን በመጥቀስ በአጠቃላይ በግለሰቦቹ ላይ ከፖሊስ ዛሬ የተረከበውን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ ለመወሰንና ክስ ለመመስረት ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገልጿል።

ግለሰቦቹ ከተጠረጠሩበት ከባድ የሙስና ወንጀል አንጻር የዋስትና መብታቸው ተነፍጎ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩለት ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት የሰብአዊ መብት ጥሰት ደርሶብናል በማለት በቃል አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን÷ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን ጠቅሰው የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸውም ነው የጠየቁት፡፡

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ ወንጀል አልፈጸምንም በማለት የተከራከሩ ቢሆንም በጊዜ ቀጠሮ ዳኞች በኩል ወንጀል ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም የሚለውን የማስረጃ ምዘና ጉዳይን በሚመለከት በመደበኛ ፍርድ ቤት የሚታይ መሆኑን ገልጸው፤ የማስረጃ ፍሬ ነገር ላይ ክርክር እንዳይደረግ ለተጠርጣሪዎቹ አስገንዝበዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ደረሰብን ስላሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት አቤቱታችሁን በጽሑፍ አቅርቡ በማለት በችሎቱ ዳኞች በኩል ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በአጠቃላይ የተነሳውን የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ በማለፍ ለዐቃቤ ሕግ 15 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version