የሀገር ውስጥ ዜና

በሐረሪ ክልል ከ”መደመር ትውልድ” መጽሐፍ በተገኘ ገቢ የ”ኢኮ ፓርክ” ሊገነባ ነው

By Amele Demsew

October 10, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል ከ”መደመር ትውልድ” መጽሐፍ ሽያጭ በተገኘ 162 ሚሊየን ብር የ”ኢኮ ፓርክ” እንደሚገነባ የክልሉ ባህል፣ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ አስታወቀ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከተጻፈው የ”መደመር ትውልድ” መጽሐፍ ሽያጭ በተገኘው ገቢ በተለምዶ “ሴላት “በሚባለው አካባቢ በ24 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ለሚገነባው የ”ኢኮ ፓርክ ” የቦታ ርክክብና የውል ስምምነት ተደርጓል።

የቢሮ ሃላፊው አቶ ተወለዳ አብዶሽ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷በክልሉ ከመጽሐፉ ሽያጭ በተገኘው ገቢ ፓርኩን ለመገንባት ተጨማሪ ገንዘብ የማፈላለግና ሌሎች ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

አሁን ላይ አጠቃላይ የዲዛይንና የቦታ መረጣ ሥራዎች መጠናቀቃቸውንም አመላክተዋል።

ኢኮ ፓርክ ለቱሪስቶች ምቹና ቀንም ሆነ ምሽት አገልግሎት የሚያገኙበት እንዲሁም የክልሉን ባህልና ቅርሶች በያዘ መልኩ እንደሚገነባም ሃላፊው አስታውቀዋል።

የፓርኩ ግንባታ በሰባት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት የሚበቃ ሲሆን÷ ለዚህም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ መገለፁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በፓርኩ የጅብ ማብላት ትርዒት ፣ጋለሪ፣ሙዚዬም፣ዘመናዊና ባህላዊ ሪስቶራንት፣ቤተ መጻህፍት፣የህጻናት መጫወቻና የኮንፍረንስ ማዕከል እንደሚያካተት ተገልጿል፡፡