Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የበጀት ዓመቱ ጥቅል ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት 7 ነጥብ 9 በመቶ እንዲሆን ይሰራል-ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የበጀት ዓመቱ ጥቅል ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት 7 ነጥብ 9 በመቶ እንዲሆን በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች በትኩረት እንደሚሰራ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡፡

ፕሬዚዳንቷ÷ የ2016 በጀት ዓመት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ ባለፈው ዓመት ጅምር ውጤት የታየበት የጸረ ሌብነት ትግል ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ የታየውን ምርታማነት በማስቀጠል ከ22 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ለማረስ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህም 810 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ነው በማብራሪያቸው ያነሱት፡፡

የመንግስት ገቢ አሰባሰብን ለማሳደግ በዚህ ዓመት ከታክስ ገቢ 441 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱንም ጠቅሰዋል፡፡

ፈታኝ የሆነውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስም ጥብቅ የፊስካል እና የገንዘብ ፖሊሲ ይተገበራል ነው ያሉት፡፡

በመጪው 3 ዓመት ውስጥ 9 ነጥብ 15 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እንደሚሰራ ጠቅሰው÷ በበጀት ዓመቱም ለ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ይሰራል ብለዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version