የሀገር ውስጥ ዜና

የ2015ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ይፋ ሆነ

By Amele Demsew

October 09, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2015ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ይፋ ሆኗል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) የ2015ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤትን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም በፈተናው ከ50 በመቶና ከዛ በላይ ውጤት በማስመዝገብ የማለፊያ ነጥብ ያመጡት 27 ሺህ 267 ተማሪዎች ወይም 3 ነጥብ 2 በመቶዎቹ ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከፍተኛ ውጤት ከተፈጥሮ ሳይንስ 649 በአዲስ አበባ ከተማ ሲመዘገብ÷ በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 533 በደብረ ማርቆስ ከተማ ተመዝግቧል፡፡

አምስት ትምህርት ቤቶች ያስፈተኗቸውን ተማሪዎችን በሙሉ ማሳለፋቸውን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

ከተፈጥር ሳይንስ ተፈታኞች ውስጥ 205 ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን÷በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 15 ተማሪዎች ከ500 በላይ ውጤት ማምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የፈተና መመሪያ እና ደንብ በመጣስ በግል 483 ተማሪዎች እንዲሁም በቡድን 376 ተማሪዎች መቀጣታቸውን አንስተዋል፡፡

የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ከባለፈው ዓመት ውጤት ጋር ሲነጻጸር መሰረታዊ ለውጥ የሌለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ነገ ከጥዋቱ 12 ጀምሮ ውጤታቸውን መመልከት እንደሚችሉም ተመላክቷል።

በመላኩ ገድፍ