ቴክ

ትውልድና ጥንቃቄን የሚሻው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም

By Amele Demsew

October 08, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘርፈ ብዙ ጥንቃቄን የሚሻው የማህበራዊ ሚዲያ እንዴት መጠቀም ይገባል?

የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ ህይዎት አዳነ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር የማህበራዊ ሚዲያና አጠቃቀሙን በተመለከተ በሰጡት ሃሳብ ፥ የማህበራዊ ሚዲያ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ትውልዱ ላይ ተጽዕኖ እያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዘመኑ የሰጠውን ቴክኖሎጂ በልኩና በተገቢው መንገድ ማስተናገድ እንደሚገባ ጠቅሰው ፤ ይህም ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን በሚገባው ልክ ለማስቀመጥ ያስችላል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም እውቀት ላይ የተመሰረት የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ማሕበረሰብን ለመገንባት የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

በዚህም ማህበራዊ ሚዲያ የእውቀት መረጣ ያስፈልገዋል ያሉ ሲሆን ፥ ማስተዋልና ቆም ብሎ መጠየቅ ይገባልም ብለዋል፡፡

የሰላም አምባሳደርና የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ አካሉ አብርሃም በበኩላቸው ፥ በአብዛኛው የማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚው ወጣቱ በመሆኑ ማሕበራዊ ሚዲያን ለበጎ ብሎም ራስን ለማሳደግ ሊጠቀመው ይገባል ሲሉ መክረዋል፡፡

ቻይናን እንደአብነት ያነሱት የሰላም አምባሳደርና የፓን አፍሪካ አቀንቃኙ ፥ ሀገሪቱ ዕውቀት ላይ የተመሰረተ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ያላት እንደሆነ ጠቅሰው ፥ ፈጠራና የሀገሪቱን ባህል በጠበቀ መንገድ እየተከወነ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ማሕበራዊ ሚዲያን ሲጠቀሙ የሚያስፈልጋቸውን መምረጥና መጠየቅ ያስፈልጋቸዋልም ነው ያሉት፡፡

ወጣቶች ሀገር የሚገባትን ሰላምና እድገት በእውቀት እየተመራ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ተስፋ ለመሆን በተግባር የሚያሳይበት ቁመና ላይ እንዲገኝ ይጠበቃል፡፡

ለዚህ ደግሞ ከማሕበራዊ ሚዲያ ተገቢ ያልሆነ ጫናዎች ተላቆ በእውቀት እንዲመራ የሁሉንም ድርሻ ይጠይቃል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምም ስርዓት ሊበጅለት እንደሚገባም ነው የመከሩት፡፡