Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አቶ ፍቃዱ ተሰማ ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አቶ ፍቃዱ ተሰማ ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

 

 

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ የሰላም፣ የአንድነት እና ወንድማማችነት ተምሳሌት ለሆነው ለታላቁ የኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

 

የኃላፊው ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል

 

ሰማይና ምድርን ውብ አድርጎ ለፈጠረው፤ ፍጥረታትን ሁሉ አቻችሎ ለሚያኖረው፣ ከዘመን ዘመን  ለሚያሸጋግረው ፈጣሪ ( ዋቃ) ምስጋና የሚቸርበት ታላቁ የኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ዋዜማ ላይ እንገኛለን፡፡

 

ይህ ታላቅ የምስጋና ፣ የይቅርታ፣ የወንድማማችነት እሴት የሚንፀባረቅበት፣ አባገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች፣ ፎሌዎች፣ ልጃገረዶች፣ ሌሎችም ወንድምና እህት ህዝቦች እና የውጭ ሀገር ዜጎች ጭምር ህብር በሆነው ባህላዊ አለባበስ ደምቀው የሚታደሙበት በዓል በጉጉት ይጠበቃልና በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ለምትኖሩ  ለኦሮሞ ህዝብ እንዲሁም ለመላው ወንድምና እህት ኢትዮጲያውያን እንኳን ለታላቁ የኢሬቻ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡

 

በነጎድጓዳማው የክረምት ወራት ሰማይና ምድሩ ጭጋግ ለብሶ አስፈሪ በሆነበት፤ ወንዞች ከአፍ እስከ ገደፍ ሞልተው ዘመድን ከዘመድ የለዩበት፤ የተደከመበት አዝመራ አሽቶ ደርሶ ከጎተራው ይግባ ይቅር ከፈጣሪ (ከዋቃ) በስተቀር ማንም እርግጠኛ በማይሆንበት እና ውጣውረድ በበዛበት፤ ተፈጥሯዊ አደጋ የሚያንዣብብበት አስቸጋሪው  ጊዜ  አልፎ  የመኸር ወራት ተስፋን አዝለው፤ በፈገገው ሰማይ፤  በብርሃን ደምቀው ሲከሰቱ መላው የኦሮሞ ህዝብ ሰለ ፈጣሪ (ዋቃ) ምህረትና ቸርነት ምስጋና ያቀርባል፡፡

 

ታዲያ በኢሬቻ ለፈጣሪ (ዋቃ) ምስጋና ለመቸር ወደ ሆራ ወይም መልካ ሲኬድ ቂም ቋጥሮ ኩርፊያን  አዝሎ ሳይሆን በፍጹም ሰላማዊና ይቅር ባይነት መንፈስ ነውና የተኮራረፈም ሆነ ቂም የቋጠረ በዓሉን ከመታደሙ በፊት ያቄመውን ልቡን በእርቅና ይቅርታ አንፅቶ ፍቅርና ወንድማማችነትን አንግሶ ነው በበዓሉ ላይ የሚታደመው፡፡

 

ለዚህም ነው ኢሬቻ የምስጋና ብቻ ሳይሆን የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የወንድማማችነት እሴት መገለጫ ድንቅ ባህል ሆኖ የሚከበረው፡፡

 

ይቅርታና ምህረት፣ ሰላምና መተሳሰብ ባለበት ሁሉ ህዝባዊ አንድነት፣ አዎንታዊ መስተጋብር የፀና ስለሚሆን ኢሬቻ ለኦሮም ህዝብም ሆነ ለሌሎች ወንድም ህዝቦች የፅኑ አንድነት መሰረት ተምሳሌት ነው፡፡

 

የኦሮሞ ህዝብ በሃይማኖት ፣ በጎሳ ፣ በቀለም፣ በእድሜ እና ፆታ ሳይገደብ በወል ማንነት ፀንቶ በየዓመቱ በይቅርታና ምህረት መንፈስ በጋራ ቆሞ በኢሬቻ ፈጣሪን (ዋቃን) ያመሰግናል፡፡

 

በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ዉጭ  በርካታ ወንድም ህዝቦች በስፋት የሚታደሙበት የወንድማማችንት እሴት ማሳያ ትልቅ  ዓለም አቀፋዊ በዓል እየሆነ ነው፡፡

 

እኛ ኢትዮጵያውያን የበርካታ ድንቃድንቅ ተፈጥሮ እና ባህል ባለቤት ነን፤ በርካቶች ያልታደሉትን ፀጋ እኛ ተችረናል፡፡

 

ለአብነት ከኢሬቻ ውጭ በየአመቱ የሲዳማ ህዝብ ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምበላላን፣ የሀድያ ዘመን መለወጫ ያሆዴን፣ የጋሞ ህዝብ ዘመን መለወጫ ዮማስቃላን፣ የጌዲኦ ብሔር ዘመን መለወጫ ደራሮን፣ የወላይታ ዘመን መለወጫ ጊፋታ፣ አሸንዳ እና በርካታ ተዘርዝረው የማያልቁ የየራሳቸው ቀለማት ያሏቸውን ህዝባዊ በዓላት በጋራ እናከብራለን፡፡

 

በብዝሃነታችን ውስጥ የሚታዩት ህብር ቀለማት የውበታችን ምንጭ እና የአንድነታችን መሰረቶች ናቸው፡፡

 

ሁላችንም የየራሳችን ቀለም ይዘን በመከባበር በጋራ ስንኖር የበለጠ እንደምቃለን፡፡ አንዳችን የሌሎቻችንን  ማንነት አክብረን በመደመር በጋራ ስንኖር ህበረ-ሀጋራዊ አንድነታችን በጽኑ መሰረት ላይ ይተከላል፡፡

 

የምንወዳት ትውልድ በቅብብሎሽ መስዋዕትነት ከፍሎ ያቆያት ኢትዮጵያችን ብልፅግናዋ ይረጋገጣል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ህብር የሆነውን ተፈጥሯዊ ማንነታችንን እንደመልካም እድል በመጠቀም ሊከፋፍሉን የሚሹ ሀይሎችን በጽናጽ ልንታገላቸው ይገባል፡፡

 

በመጨረሻም ኢሬቻ ስለ ሰላም ፣ይቅርታ ፣ አንድነት፣  ወንድማማችነት ብቻ እየተሰበከ ለፈጣሪ (ዋቃ) ቸርነት ምስጋና የሚዥጎደጎድበት ታላቅ በዓል ነው፡፡ ይህ ሰላማዊ በዓል ሰላማዊነቱ ተረጋግጦ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ ነው፡፡

 

በዓሉ በሰላማዊና በይቅር ባይነት መንፈስ ለፈጣሪ (ዋቃ) ምስጋና የሚቸርበት ቢሆንም ህዝባዊ በዓላትን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እኩይ አላማቸውን ለማሳካት የሚጥሩ  አካላትን በአይነቁራኛ መከታተል ያስፈልጋል፡፡

 

በዓሉ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር እስከ ዋዜማው ከፍተኛ ጥረት ስታደርጉ  ለነበራችሁ ለመላው የፀጥታ አካላት ፣ ለአባ ገዳዎች፣ ለሀደ ሲንቄዎች፣ ለፎሌዎች፣ ለሚዲያ ተቋማት፣እንዲሁም በየደረጃው ለምትገኙ አመራሮቻችን ምስጋናዬን እያቀረብኩ ታላቁ የኢሬቻ በዓል በፍፁም ሰላማዊ ሂደት ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር በድጋሚ በተለመደው ቁርጠኝነት የድርሻችሁን እንድትወጡ አደራ ማለት እወዳለሁ፡፡

 

በድጋሚ እንኳን ለኢሬቻ በዓል ዋዜማ አደረሳችሁ፡፡

Exit mobile version