የሀገር ውስጥ ዜና

ሙያቸውን የሚያከብሩ መምህራንን ለማፍራት በትኩረት ይሰራል – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

By Amele Demsew

October 05, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ትምህርት ሚኒስቴር ሙያቸውን የሚያከብሩና በማህበረሰቡ ዘንድ የሚከበሩ መምህራንን ማፍራት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የምስረታ መርሐ ግብር የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)ን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተከናውኗል፡፡

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ÷ ዩኒቨርሲቲው የሀገራችንን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡

በሞራል ጠንካራ መሠረት ያላቸው፣ ሙያቸውን የሚያከብሩና በማህበረሰቡ ዘንድ የሚከበሩ መምህራንን ለማፍራት በሚደርገው ጥረት ሚኒስቴሩ የድርሻውን እንደሚወጣም ነው የተናገሩት፡፡

በዚህም ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ብቁ መምህራንን ለማፍራት በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ ዩኒቨርሲቲው የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት ችግር ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላት በጋራ እንዲሰሩ መጠየቃቸውን ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡