አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር ውስጥ ወረቀትና የወረቀት ውጤቶች ማምረት በመቻሉ 77 በመቶ የሚሆነው የወረቀት አቅርቦት ፍላጎትን መሸፈን መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ወረቀትና የወረቀት ውጤቶች አምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር ለመፍታት ያለመ ውይይት ከባለድርሻ አካላትና ከአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር አካሂዷል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የወረቀት ውጤቶችን ማምረት በመቻሉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መቀነስ ተችሏል።
አሁን ላይ የፍላጎቱ 22 ነጥብ 5 በመቶ የወረቀት ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ አመልክተዋል።
ከ30 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ በሚገኙባት ሀገር ውስጥ ወረቀትና የወረቀት ውጤቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆኑን አፅዕኖት ሰጥተዋል፡፡
አምራች ኩባንዎች ለወረቀትና ወረቀት ውጤቶች የሚያገለግሉ ተረፈ ምርቶችን መልሶ የመጠቀም አቅማቸው ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ አምራች ኢንዱስትሪዎች በመደጋገፍ ችግሩን ሊፈቱ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በዚህ ረገድ መንግስት የዘርፉን ችግር ለመፍታት ቁርጠኛ ነው ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡