Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

26 ሀገራት የሚሳተፉበት የእንቆጳ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ26 ሀገራት ተወካዮች የሚሳተፉበት የእንቆጳ ጉባኤ ከፊታችን ጥቅምት 1 ቀን ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ጉባዔው ኢትዮጵያ በዲጅታል ኢኮኖሚ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም እና መንግስትና የግሉን ዘርፍ በማስተሳሰር የሥራ ፈጣሪነት ምህዳርን ለማስፋት ያለመ ነው ተብሏል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ ንጉሡ ጥላሁን÷መድረኩ የዘርፉ ተዋናዮች በማስተሳሰር በኢትዮጵያ የኢንተርፕረነርሺፕ ስነ-ምህዳር ለማስፋት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በዲጅታል ኢኮኖሚ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ለተቀሪው ዓለም ለማስተዋወቅ እንደሚያስችል ነው የገለጹት፡፡

በመድረኩ የዘርፉ ምሁራን፣ፖሊሲ አውጪዎች፣ አህጉራዊ ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች፣ የልማት አጋር አካላት፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ሥራ ፈጣሪዎችና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ፡፡

በተጨማሪም የፋይናንስ ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት፣ ኢንቨስተሮች፣ በፍሪላስንጊ እና ጊግ ኢኮኖሚ በንቃት የሚሳተፉ የግል ድርጅቶችና ስታርታፖችን ጨምሮ የ26 ሀገራት ተወካዮች የሚሳተፉ ይሆናል፡፡

ጉባኤው በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ጥቅም 1 እና 2 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version