አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ’ክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢንሸቲቭ ’ ለማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ህክምና አገልግሎት የሚውሉ 50 በሙቀት ሃይል የሚያክሙ ተርማል አብሌሽን ማሽኖችን ለጤና ሚኒስቴር አስረክቧል፡፡
’ክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢንሸቲቭ ’ ለረዥም ጊዜ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመደገፍ የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲኖር እያገዘ መቆየቱን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ በኢትዮጵያ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በርካታ እናቶችን እያሳጣ ያለውን የማህፀን በር ካንሰር ለመከላከል የሚያገለግል ማሽን በመለገሱም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ማሽኑ በቀላሉ ተንቀሳቃሽ በመሆኑ በየትኛውም አካባቢ በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢዎችና ተፈናቃዮች ባሉበት አካባቢ አገልግሎት ለመስጠት አመቺ መሆኑን ጠቁመዋል።
የማህጸን በር ካንሰርን ክትባት በመከተብ፣ የተጠናከረ ምርመራና ልየታ በማድረግና ቅድመ ካንሰር ምልክት ያላቸውን ደግሞ በማከም መከላከል እንደሚቻልም ዶክተር ደረጀ አስገንዝበዋል፡፡
ህክምናው ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች አገልግሎቱን ለመስጠት የተለገሱት 50 ተርማል አብሌሽን ማሽኖች አገልግሎት ላይ ካሉት ማሽኖች ጋር ተደምረው አቅምን የሚያሳድጉ መሆናቸውን በመግለጽ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢንሸቲቭ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ራሄል በለጠ በበኩላቸው÷ ድጋፉ ካንሰር ከመከሰቱ በፊት በማከም ህይወት መታደግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማረጋገጣቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በሀገራችን በ1 ሺህ 330 ጤና ተቋማት ለ1 ነጥብ 3 ሚሊየን እናቶች የቅድመ ካንሰር ምርመራ የተደረገ ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት በፈረንጆች 2030 ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት ከ7 ሚሊየን በላይ እናቶችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡