Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በመዲናዋ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል አስፈጻሚ አካላት ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የዋጋ ንረትን በመከላከል የኑሮ ውድነትን ለማቃለል አስፈጻሚ አካላት ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የምክር ቤት አባላት አሳሰቡ።

የመዲናዋን ነዋሪዎች የወከሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተዋል።

የህዝቡን ችግሮች ለመፍታትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ስለተከናወኑ ተግባራትም የምክር ቤቱ አባላት በስፋት መክረዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ እያሱ ኤሊያስ (ፕ/ር ) እንዳሉት÷ በውይይቱ ከኑሮ ውድነት በተጨማሪ ሰላምና ጸጥታ፣ የስራ እድል ፈጠራና የወጣቶችን ተጠቃሚነት፣ አገልግሎት አሰጣጥና የመሰረተ ልማት ጉዳዮች ተነስተዋል።

በዚህም ችግሮቹን ለመፍታት በተለይም አስፈፃሚው አካል ብዙ ስራ ይጠበቅበታል ብለዋል።

ሌላኛው የምክር ቤት አባልና የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሀነመስቀል ጠና (ዶ/ር)፤ የኑሮ ወድነትን ለማቃለል ህገ ወጥነትን በጋራ መከላከልና ችግሮችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት።

የሰላምና ጸጥታም በመንግስት ጥረት ብቻ የማይሳካ በመሆኑ የሁሉም ሃላፊነት መሆን አለበት ሲሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ ጊዜያዊ ዋና ስራ አስፈፃሚ አበበ ተቀባ÷ የነዋሪውን ፍላጎት ለማሟላት የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም በቂ ባለመሆናቸው በቀጣይ ለተሻሉ ስራዎች ተዘጋጅተናል ብለዋል።

Exit mobile version