የሀገር ውስጥ ዜና

ብልጽግና ፓርቲ ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

By Amele Demsew

October 03, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

በሀገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳታፊ ለመሆን ዝግጅት መድረጉንም አቶ አደም ፋራህ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አመራሮች ጋር የኮሚሽኑን የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ ውይይት አድርገዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ኮሚሽኑ እስከ አሁን ያከናወናቸው ሥራዎች በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

በመድረኩም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በውይይይት መድረኩ የተሳተፉት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፤ ኮሚሽኑ የተሳካ ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ እስካሁን ያከናወናቸው ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተለይም ሀገራዊ ምክክሩ አካታችና ሁሉን አሳታፊ ለማድረግ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ለማረጋገጥ የተሄደበት ርቀትና አጠቃላይ ጥረቶች የሚደነቁ መሆናቸውን ነው ያነሱት።

በቀጣይም “ከማን ምን ይጠበቃል” የሚለውን በመለየትና ቀሪ ሥራዎችን በተሳካ መልኩ ለማከናወን ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተወያየ መሆኑን በገለጻው መረዳት መቻላቸውን ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንደሚያስችልና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም በማስፈን የብልጽግና ጉዞዋን ለማፋጠን እንደሚያስችል ከፓርቲው አባላት ጋር የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።

ፓርቲው እንደ አንድ ባለድርሻ አካል በሀገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳታፊ ለመሆንና ሀገራዊ ምክክሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ የምክክር ውጤቱን ገቢራዊ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት ማድረጉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡