የሀገር ውስጥ ዜና

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት ተስማማ

By Amele Demsew

October 03, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ በ2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና ኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

ዩኒቨርሲቲዉ በማስተማር ሂደቱ በዋናነት ትኩረት የሚያደርግባቸው የክልል አመራርና ሰራተኞች አቅም ግንባታ፣ የተቋማት የለውጥ ስራ እና መንግስታዊ ያልሆኑ የግል ተቋማት አቅም ግንባታ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ገረመው ሁሉቃ÷ ዩኒቨርሲቲው ጥናትና ምርምር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር መስራቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለሌሎች አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግና ለማስተዋወቅ እድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል፡፡

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በበኩላቸው÷ ሚዲያው ለህበረተሰቡ የተጣራና ተዓማኒ መረጃ ለማቅረብ ዘወትር እየተጋ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ከዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ መስራቱ ጉልህ የሆነ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።

ኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ከስድስ ዓመት በፊት ከኢንስቲትዩት ወደ ዩኒቨርስቲነት ያደገ ብቸኛው የክልል ዩኒቨርሲቲ ነው።

በማህሌት ተክለብርሃን