Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በስነምግባር ግድፈት የተከሰሱ 24 ጠበቆች ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ በ2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትህ ሚኒስቴር የፌደራል ፍርድ ቤቶች የስነምግባር ኮሚቴ በስነምግባር ግድፈት ክስ የቀረበባቸው 24 ጠበቆችን መርምሮ ጥፋተኛ በማለት ቅጣት ጥሎባቸዋል።

ከ24ቱ ተከሳሾች መካከል 18ቱ የጥብቅና ፍቃዳቸውን በወቅቱ ባለማደስ የተከሰሱ ሲሆን ቀሪዎቹ ግን በባለጉዳይ በቀረበባቸው የስነምግባር ግድፈት ክስ ነው ጥፋተኛ ተብለው ቅጣት የተጣለባቸው፡፡

የፍትህ ሚኒስቴር የጥብቅና ፍቃድ አሰጣጥ አስተዳደርና የነጻ ህግ ድጋፍ አገልግሎት ዳሪክተር አቶ ፍቃዱ ደምሴ ለፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በስነምግባር ግድፈት ክስ የቀረበባቸው 46 ጠበቆች ነበሩ።

ክስ ከቀረበባቸው ጠበቆች መካከል 24ቱ የቀረበባቸው ክስ ተመርምሮ ጥፋተኛ በመባላቸው ቅጣት እንደተጣለባቸው ገልጸው፤ ቀሪዎቹ ነጻ ተብለዋል።

ጥፋተኛ ከተባሉት 24 ጠበቆች ውስጥ ደግሞ 18ቱ በወቅቱ የጥብቅና ፍቃዳቸውን ባለማደስ በስነምግባር ግድፈት የተከሰሱት በገንዘብ እንዲቀጡ ተወስኗል።

በተመሳሳይ በባለጉዳይ የስነምግባር ግድፈት ክስ የቀረበባቸው አራት ጠበቆች በገንዘብ እንዲቀጡ የተወሰነ ሲሆን አንድ ጠበቃ ደግሞ ለ3 ወራት ከጥብቅና ሙያው እንዲታገድ ተወስኗል።

እንዲሆም ሌላኛው አንድ ጠበቃ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው ኃላፊው ገልጸዋል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version