የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ “ብሪክስ”ን መቀላቀል የደቡብ-ደቡብ ትብብርን እንደሚያጠናክር ተጠቆመ

By Alemayehu Geremew

October 03, 2023

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ “ብሪክስ”ን መቀላቀል የደቡብ-ደቡብ ትብብርን እንደሚያጠናክር በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር አብዱላ ገለጹ፡፡

ዓለማችን ዘላቂ የማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንድታስመዘግብ በማገዝ ረገድም የኢትዮጵያ ወደ ኅብረቱ መቀላቀል ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡

አምባሳደር ጀማል በከር በፓኪስታን የብራዚል አምባሳደር ኦሊንቶ ቪዬራ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ስለ ኢትዮጵያ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት፣ እምቅ የተፈጥሮ ሐብት እና ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታን በተመለከተ አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ “ብሪክስ”ን መቀላቀሏየቡድኑን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከማሳደጉም በላይ ተቋማዊ አቅሙን እንደሚያጎለብተውም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)÷ በግብርናው ዘርፍ፣ በግብርና ግብዓቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአይሲቲ እንዲሁም በቱሪዝም ላይ ባካሄዱት የለውጥ አብዮት ኢትዮጵያ ዓለማችን ወደምትከተለው ዘመናዊ የምጣኔ ሐብት መንገድ መግባቷንም ጠቁመዋል።

በ”ብሪክስ” አባል ሀገራት መካከል የሚኖረው ትብብር÷ ምጣኔ-ሐብታዊ ውህደትን፣ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግርን፣ የጋራ የከባቢ እንክብካቤን፣ ጥራት ያለው የትምህርትና የጤና ተቋማት ተደራሽነትን እንዲሁም የአባል ሀገራቱን በመሠረተ ልማት የመተሳሰር ፍላጎት እንደሚያሳልጥም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላምና ዘላቂ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸው፤ በትብብር ለማደግ ያላትንም ጠንካራ አቋም አስምረውበታል።

ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራቾች አንዷመሆኗንና በድርጅቶቹ ውስጥ ያላትን ታሪካዊ ሚናም አስረድተዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በዓለም ላይ ፍትህ፣ ሰላምና ደኅንነት እንዲሰፍን ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የብራዚል አምባሳደር ኦሊንቶ ቪዬራ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በፍጥነት እየተለዋወጠ ባለው ዓለም ውስጥ አወንታዊ ሚና መጫወቷ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

የደቡብ-ደቡብ ትብብርም በዓለም አቀፉ መድረክ እኩል አሳታፊ ማሕበራዊና ምጣኔ ሐብታዊ ልማትን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

ዓለም ከጂኦ-ፖለቲካዊ እሳቤ ወደ ጂኦ-ኢኮኖሚያዊ ውኅደት የመግባት ፍላጎት እያዘነበለች ነው ማለታቸውን በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመልክቷል።