Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

“አንድ ቤተሰብ ለአንድ ህፃን” በሚል መሪ ቃል ለ100 ህጻናት ዘላቂ ድጋፍ መስጠት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 22 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ስምምነቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የህብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና የኤም ደብሊው ኤስ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ማናዬ ሰንደቁ ተፈራርመውታል።

ከአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰብ 100 ህፃናት እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ለማስተማርና ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ልዩ የቀጣይ ትውልድ ግንባታ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመርሐ-ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ እናት ልጇ በአካል እና በአዕምሮ ሲያድግና ሲጎለብት ከማየት በላይ የሚያስደስታት እንደሌለ ሁሉ የከተማ አስተዳደሩም ለዚህ በተለያዩ ተግባራት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

“ሰው ተኮር ፖሊሲያችን የሚሰራው ለሰው ነው” ያሉት ከንቲባ አዳነች ይህም ከመንግስት ዋነኛ መርሆዎች አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባን በአፍሪካ ህፃናትን ለማሳደግ ምርጧ ከተማ ለማድረግ ሰፋፊ ስራዎችን እየሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።

ከንቲባ አዳነች አክለውም በመንግስት የተያዘው ትውልድን መገንባት፣ በከተማዋ ደግሞ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶች በመሰራት ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ዛሬ 100 ህፃናትን እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ለማስተማርና ለመደገፍ ቃል የገቡት አቶ ማናዬ ሰንደቁ የከተማዋን በጎ ራዕይ በመጋራት ይህንን ትልቅ ሀላፊነት በመውሰዳቸውም ምስጋነናአቅርበዋል።

በዛሬው እለት የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ ከሆኑት በተጨማሪ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በክረምቱ 330 ህፃናት ከ3 ወር እስከ 3 ዓመት የድጋፍ ትስስር እንደተፈጠረላቸው የከተማው ኮሙኒኬሽን መረጃ  ያመላክታል።

በአጠቃላይ 430 ህፃናት የዚህ በጎ መርሐ ግብር ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

 

Exit mobile version