ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ ዩክሬንን መርዳት እንደምትቀጥል አስታወቀች

By Alemayehu Geremew

October 02, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች፡፡

ምንም እንኳን ጉምቱ የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች አሜሪካ ቅድሚያ መሥጠት የሚገባትን የራሷን ጉዳዮች ቸል ብላለች እያሉ ቢገኙም ባይደን ግን አሁን ከዩክሬን የባሰ ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ የለንም ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱም ቀልዱን ትቶ በአስቸኳይ ለዩክሬን የሚላከውን ልዩ ድጋፍ እንዲያጸድቅላቸው ነው ያሳሰቡት፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የሪፐብሊካኑ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ኬቨን ማካርቲ ዩክሬንን ለመርዳት የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ መናገራቸውንም አር ቲ ዘግቧል፡፡

የአሜሪካ ወዳጆች እንዲሁም የአሜሪካ እና የዩክሬን ሕዝቦች ÷ ኪየቭን ጥለን የትም እንደማንሄድ ፣ ድጋፋችንም እንደማይቋርጥ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ ብለዋል።

በሌላ በኩል የሩሲያና ዩክሬንን ማብቂያ የሌለው ጦርነት የተመለከቱ የአሜሪካ ጉምቱ ኅግ አውጪዎች ለኪየቭ የሚላከው ገንዘብም ሆነ የዓይነት ድጋፍ ትርጉም የሌለው ነው በሚል እንዲቆም ይሞግታሉ፡፡

በዚህም ምክንያት ምክር ቤቱ ባይደን የሚያቀርቡትን ለዩክሬን የሚደረግ የድጋፍ ጥያቄ ለማጽደቅ አስቸጋሪ እያደረገባቸው ይገኛል፡፡

አፈ-ጉባዔ ኬቨን ማካርቲ በበኩላቸው÷ ሪፐብሊካኑ ዩክሬንን ለመርዳት ቁርጠኛ ቢሆኑም የውስጥ የደኅንነት ጉዳያችንን ግን መዘንጋት የለብንም ብለዋል፡፡

የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ሐሳብም መደመጥ እንዳለበት ነው በአጽንኦት የተናገሩት፡፡

ይሄን የተመለከቱት የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ዲፕሎማት ጆሴፍ ቦሬል ዕሑድ ዩክሬንን በጎበኙበት ወቅት ÷ ለዩክሬን የሚደረገው ወታደራዊ ድጋፍ በአሜሪካ ውሳኔዎች ላይ ብቻ የተመሠረተ እንደማይሆን አንስተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ብራስልስ ወታደራዊ እና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን ለዩክሬን ማድረግ እንደምትቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡