ጤና

የኤች አይ ቪ እና ኤድስ መረጃ

By Meseret Awoke

October 01, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኤድስ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ባለባቸው ሰዎች ላይ ሊፈጠር የሚችል በሽታ ነው።

በፀረ-ኤች አይ ቪ መድሐኒቶች የሚደረግ ሕክምናም ኤድስን በኤች አይ ቪ በተያዙ ሰዎች ላይ እንዳይፈጠር ይከላከላል።

ኤች አይ ቪ በሽታ የመከላከል አቅምን የሚጎዳ ቫይረስ ሲሆን ፥ ያልታከመ ኤች አይ ቪ በሲዲ 4 ህዋሳቶች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡

በጊዜ ሂደት ኤች አይ ቪ ሲዲ 4 ህዋሶችን ሲገድል፣ ሰውነት ለተለያዩ ዓይነት በሽታዎችና ካንሰሮች የመጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነም ይገለጻል፡፡

ኤች አይ ቪ በደም፣ የፊንጢጣ እና የብልት ፈሳሽ እንዲሁም የጡት ወተት ምክንያት ይተላለፋል፡፡

በአንጻሩ ቫይረሱ በአየር፣ በውሃ ወይም በማንኛውም የማሕበራዊ ሰላምታዎችና ግንኙነቶች በመሳተፍ አይተላለፍም፡፡

ኤች አይ ቪ እራሱን ወደ ሴሎች ዲ ኤን ኤ ውስጥ ስለሚያስገባ እስካሁን ይሕን ቫይረስ ከሰውነት የሚያስወግድ መድሃኒት አልተገኘም፡፡

ሆኖም ብዙ ተመራማሪዎች ሙከራ እያደረጉ እንደሆነም ይገለጻል፡፡

በፀረ ኤች አይ ቪ ሕክምና በአግባቡ በመውሰድ ኤች አይ ቪን መቆጣጠርና ከቫይረሱ ጋር ለብዙ ዓመታት መኖር እንደሚቻልም ነው የሚነገረው።

የኤች አይ ቪ የመጀመሪያ ምልክቶች ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ እብጠት፣ የህመም ስሜት፣ የቆዳ ሽፍታ፣ በጉሮሮ መዘጋት፣ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽና የሆድ ህመም ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህ ምልክቶች እንደ ኢንፍሉዌንዛ ካሉ የተለመዱ ሕመሞች ጋር የሚመሳሰሉ ቢሆንም ሕክምና በማግኘት ራስዎን የጤና ሁኔታ ማወቅ እንደሚያስፈልግ ኽልዝላይን ይመክራል፡፡

በኤች አይ ቪ ከተያዙ ከወራት በኋላ ራስ ምታት እና ሌሎች ህመሞች፣ እብጠት፣ ተደጋጋሚ ትኩሳት፣ የምሽት ላብ፣ ድካም፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ ተቅማጥ፣ ክብደት መቀነስ፣ የቆዳ ሽፍታ፣ ተደጋጋሚ ኢንፌክሽኖችና የሳንባ ምች ይገኝበታል፡፡

በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ስርጭት እየጨመረ እንደሆነ ይገለጻል፤ በዚህም እንደከዚህቀደሙ ለበሽታው ትኩረት በመስጠት መከላከል እንደሚገባ የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡