Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኦሮሚያ ክልል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማዕከል በማድረግ የተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች አበረታች ውጤት አስመዝግበዋል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የህብረተሰብቡን ተጠቃሚነት ማዕከል በማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውና የፌዴራል እንዲሁም የክልሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ባለፉት ሁለት ቀናት በጅማና አካባቢው ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ወቅት÷በክልሉ የመደመር ዕሳቤን ማዕከል በማድረግ አራት መሰረታዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት፣ ወደ ውጭ የሚላክን ምርት ማሳደግ፣ የስራ እድል ፈጠራን ማሻሻል መሆናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ በመኸር እና መስኖ የሚለማውን የመሬት ሽፋን በማሳደግ ረገድ ውጤታማ ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡

ከአማራ ክልል ተሞክሮ በመውሰድ ከሶስት ዓመት በፊት የተጀመረው የሩዝ ምርትም ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በሩዝ ምርት ራስን ከማቻል ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተጀመረውን ስራ በማገዝ ረገድ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከ5 ቢሊየን በላይ የቡና ችግኞች እንደተተከሉም ጠቅሰው÷አርሶ አደሩ የቡና ምርትን በቀጥታ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን አክለዋል፡፡

በቀጣይም የምርት ጥራት ላይ ትኩረት በማድረግ የወጭ ንግድን ማሳደግ ላይ ያተኮሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በክልሉ ከፍተኛ የመልማት አቅም መኖሩን ገልጸው ይህንን አቅም በቴክኖሎጂ በማገዝ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ይህንን የአርሶ አደሩን ትጋት በአግባቡ በመደገፍ ጠንክሮ መስራት ከተቻለ በአጭር ጊዜ የላቀ ውጤት እንደሚረጋገጥም ነው የተናገሩት።

 

 

Exit mobile version