አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሠራ አውሮፕላን የመጀመሪያውን የተሳካ ዓለምአቀፍ በረራ አደረገ፡፡
በረራውን ወደ ካናዳ ሞንትሪያል ያደረገው አውሮፕላን መንገደኞችን እና ጭነት ለማጓጓዝ በሚያስችል መልኩ መሠራቱም ተነግሯል፡፡
“ቤታ ቴክኖሎጂስ” በተሠኘው ዓለምአቀፍ የቴክኖሎጂ ድርጅት ዕውን የሆነው ይህ አውሮፕላን ሞንትሪያል በሥኬት ሲያርፍ በዓለምአቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ዋና ጸኃፊ ዩዋን ሁዋን ካርሎስ የሞቀ አቀባበል ተደርጎለታል ነው የተባለው፡፡
ዋና ጸኃፊው ድርጅታቸው በአቪየሽኑ ዘርፍ የሚከሰቱ እንዲህ ያሉ አዲስ ዕይታዎችን እና ፈጠራዎችን እንደሚያበረታታ ገልጸዋል።
ፈጠራው የዓየር ንብረት ብክለትን ከመግታት አንጻር የሚደረገውን ጥረት ከመደገፍ አንጻር አጋዥ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አውሮፕላኑ በሚያርፍበት ጊዜ የዓለምአቀፉ ሲቪል አቪየሽን ድርጅት የአየር መንገድ አሰሳ ቢሮ ዳይሬክተር፥ ሚሼል ሜርክል፣ የ”ኤሮ ሞንትሪያል”ፕሬዚዳንት እና ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ሜላኒ ሉሲየር ተገኝተው ማየታቸውን ዓለምአቀፉ ሲቪል አቪየሽን አስነብቧል።