የሀገር ውስጥ ዜና

የመስሕብ ስፍራዎችን በአግባቡ ጠብቆ በማስተዋወቅ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል- አቶ ጌታቸው ረዳ

By Amele Demsew

September 28, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የሚገኙ የቱሪዝም የመስህብ ስፍራዎችና ቅርሶች በአግባቡ ጠብቆ በማስተዋወቅ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን እየተደረገ ባለው ጥረት ሁሉም ድርሻ ሊወጣ ይገባል ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ገለፁ።

የደመራ በዓል በዓዲግራት ከተማ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በተገኙበት ዛሬ በደማቅ ሥነሥርዓት ተከብሯል።

አቶ ጌታቸው በዚሁ ጊዜ የተገኘውን ሰላም ተጠቅመን በዓሉን ማክበር እንደቻልነው ሁሉ፤ በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን እየጠበቅን የቱሪስት መዳረሻ ልናደርጋቸው ይገባል ብለዋል።

የትግራይ መልሶ ግንባታን ለማፋጠን ከፌዴራል መንግሥት ጋር የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ጌታቸው አረጋግጠዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የህዝብ ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶችና ምሁራን የችግር የመፍትሄ አካል ሆኖው ድርሻቸው እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የክብረ በዓሉ ታዳሚዎች በበኩላቸው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከመንግሥት ጎን ሆነው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በዓዲግራት ከተማ በተከበረው የደመራ በዓል ላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና የሃይማኖትአባቶች ተገኝተዋል።