አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ላዳ መኪኖች በኢትዮጵያ ተመርተው ለአፍሪካ ገበያ ሊቀርቡ መሆኑ ተነገረ፡፡
የሩሲያዎቹን ላዳ መኪኖች በኢትዮጵያ ለማምረት የሚያስችል ሥምምነት መደረሱን ታስ የተሰኘው የሩሲያ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
ከስምምነት ላይ የደረሰው አቭቶቫዝ የተሰኘው መንግስታዊው የቤት መኪና አምራች ኩባንያ መሆኑ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱት ላዳ መኪኖች÷ ሱዳንን፣ ደቡብ ሱዳንን እንዲሁም ኬንያን እና ሶማሊያን ጨምሮ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ይላካሉም ተብሏል፡፡
መኪኖቹን በቅርብ ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ማምረት እንደሚጀመር የተጠቆመ ሲሆን፤ ሌሎች የሩሲያ መኪና አምራች ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ የመኪና መገጣጠም ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ እንደሆነ ተጠቁሟል።
በጉዳዩ ላይ ሁለት የሩሲያ መኪና አምራች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለመሥራት እየመከሩ መሆኑም ተገልጿል፡፡