የሀገር ውስጥ ዜና

በግጭት ንብረታቸው ለወደመባቸው የጋሞ ተወላጆች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ

By Meseret Demissu

May 14, 2020

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰበታ ኬንቴሪና ወለቴ አካባቢ ቀደም ሲል በነበረ ግጭት ንብረታቸው ለወደመባቸው የጋሞ ተወላጅ ቤተሰቦች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገላቸው።

የድጋፉ አስተባባሪ አቶ አክሊሉ ተስፋዬ “መረዳዳታችን የአንድነታችን ማህተም” በሚል እሳቤ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን “ጎ ፈንድ ሚ” በመክፈት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ገንዘቡ የጋሞ አባቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት ዛሬ ተጎጂዎቹ ተረክበዋል።

ድጋፉ ከፍተኛ የንብረት ውድመት ደርሶባቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች  መሰጠቱ ነው የተነገረው።

በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የጋሞ አባቶችም “የሞተ ሰው አይድንም። ነገር ግን ይህ ድጋፍ እንደማዳን የሚቆጠር ነው” ብለዋል።

ድጋፉን ላደረጉና ላስተባበሩ አካላት አመስግነዋል።መርቀዋል።

አቶ አክሊሉ በዚሁ ወቅት ዜጎቹ መጠለያ አጥተውና ልጆቻቸውን ይዘው ጎዳና ላይ መውጣታቸውን በመመልከታቸው ድጋፉ ለማድረግ መነሳሳታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የተፈናቃዮቹ ችግር እየተባባሰ መምጣቱም ለድጋፉ ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

የማስታወቂያ ባለሙያው አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ “ችግር በማንኛውም አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል ተባብሮና ተጋግዞ ማለፍ ግን የሁላችንም ኃላፊነት ነው” ብሏል።

ድጋፉ መተጋገዝን፣ መተባበርንና አለኝታነትን ያመላከተ ተግባር መሆኑንም ገልጿል።

ድጋፉን ላስተባበሩ አካላት የእውቅና ሰርተፊኬት በመርከቱን ኢዜአ ዘግቧል።

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።