ቴክ

ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ንባብ ስርዓት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

By Meseret Awoke

May 14, 2020

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ንባብ ስርዓት ተግባራዊ ሊደረግ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ።

ዘመናዊ የቆጣሪ ንባብ መሳሪያ(Common meter reading instrument) በመተግበር የቆጣሪ ንባብ ጥራት ችግርንና ግምታዊ አሞላልን ለማስቀረት የሚያስችል ነው ተብሏል።

ቴክኖሎጂው በ416 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ወጪ የተገዙ መሳሪያወች የሚተገበር ሲሆን፤ ሙሉ ለሙሉ ወደ ትግበራ ከመግባቱ በፊት ከግንቦት ወር አጋማሽ ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ በተመረጡ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት በሙከራ ደረጃ ይተገበራል።

የዘመናዊ የቆጣሪ ንባብ ሂደቱ በሚተገበርበት ወቅት የማንበቢያ መሳሪያው የቆጣሪ አንባቢው ደንበኛ ቤት መድረስ አለመድረሱ በጂ.ፒኤ.ስ (GPS) የሚያረጋግጥ ነው።

ይህም የቁጥጥር ስርዓቱ በማጠናከረ ብልሹ አሰራርን የሚከላከል ሲሆን፥ የቆጣሪ አንባቢ በደንበኛ ቤት በአካል ተገኝቶ ትክክለኛ ንባብ መውሰዱ ወይም አለመውሰዱን ማረጋገጥ የሚያስችል ነው።

በተጨማሪም ቴክኖሎጂው በራሱ የሚያነብ፤ በእጅ ሲነበብ የሚፈጠሩ ስህተቶችን የሚያስቀርና በንባብ ወቅት ምን ያህል ደንበኞችን ተደራሽ መደረጉንም ማሳወቅ የሚያስችል ነው።

ተቋሙ የCMRI ዘመናዊ የንባብ ስርዓት በሚተገብርበት ወቅት ከንባብ ጋር በተያያዘ የሚፈጠር ብክነትና ብልሹ አሰራር በከፍተኛ ሁኔታ ለመቅርፍ ያስችለዋል ተብሎ ይታመናል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትክ አገልግሎት ካሉት አጠቃላይ ደንበኞች ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት የድህረ ክፍያ ተጠቃሚ 2ነጥብ 48 ሚሊዮን መድረሱን ነው የገለጸው።