ዓለምአቀፋዊ ዜና

የጸጥታው ምክር ቤት ግጭቶችን ለመከላከልና ሰላም ለማረጋገጥ ስር-ነቀል ማሻሻያ እንዲያደርግ ተጠየቀ

By Amare Asrat

September 23, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ጸጥታው ምክር ቤት ግጭቶችን አስቀድሞ ለመከላከልና የዓለምን ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል ስር-ነቀል ማሻሻያ እንዲያደርግ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ጠየቁ።

 

ፕሬዚዳንቱ ኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው የተመድ 78ኛው ጠቅላላ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የጸጥታው ምክር ቤት ሃላፊነቱን በመወጣት ረገድ ውጤታማ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

 

ምክር ቤቱ ዴሞክራሲያዊነት የጎደለው እና ስንኩል ሲሉ አጥብቀው ኮንነውታል።

 

አሁን ላይ የዓለም የሠላም እና የደኅንነት ሥርዓት መውደቁን በማመላከት፤ ምክር ቤቱ የተሰጠውን ግጭቶች እንዳይከሰቱ የመከላከልና የዓለምን ሠላም የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዲወጣ ሥር-ነቀል ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

 

ግጭቶችን ለመከላከልና እየተከሰቱ ላሉትም ዕልባት ለመሥጠት ሁሉን የሚያሳትፍ ምኅዳር የለም፤  በዚህም የተነሳ ሀገራት ያላቸው መተማመን እየተሸረሸረ መጥቷል ሲሉ ገልጸዋል።

 

በጸጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ሀገራት ፍትሃዊ ውክልና እንደሌላቸው ጠቅሰው፤ የጸጥታው ምክር ቤት እንደ ተቀሩት ዓለም አቀፍ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሁሉ የአፍሪካንም ድምፆችና አመለካከቶች በተሻለ መልኩ ማንጸባረቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

 

አፍሪካ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ጥያቄዋን በማቅረብ በኩል ከፈረንጆቹ 2005 ጀምሮ በፅናት መታገሏንም አስታውሰው፤ አፍሪካ ፍትሃዊ ውክልና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደምትቀጥል ገልጸዋል።