አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስካሁን ባለው ሂደት 600 ሚሊየን ብር ይወጣባቸው የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካቱን የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስታወቀ፡፡
ፓርኩ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ላይ እየሰራ መሆኑን እና በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ 19 የማምረቻ ሼዶች ወደ ምርት መግባታቸውን የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ ጉልላት አበበ ተናግረዋል፡፡
14 ኩባንያዎች በፓርኩ ውስጥ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው÷ ኩባንያዎቹ በሀገር ውስጥ ካሉ ድርጅቶች ጋር 300 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የንግድ ትስስር ፈጥረዋል ነው ያሉት፡፡
የአምራች ዘርፉ ሀብት በመፍጠር ዙሪያ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ወደ አምራች ዘርፉ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ፓርኩ ለ8 ሺህ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ባሻገር ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር እገዛ እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
የጃፓን፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ኖርዌይ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች እና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች በፓርኩ የተሰማሩ ሲሆን÷ በዋናነት በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ፣ በቀለም እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች መሰማራታቸው ተገልጿል፡፡