Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሕብረቱ የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒሌነን ገለጹ፡፡

78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ “ሰላም፣ ብልጽግና፣ ለውጥና ዘላቂነት” በሚል መሪ ሀሳብ በኒው ዮርክ እየተካሄደ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጉባኤው ጎን ለጎን ከአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ÷በሁለቱ ወገኖች የጋራ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያ ሰላምን በማጽናት ሂደት ውስጥ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች የሚደነቁ መሆናቸውን ኮሚሽነር ጁታ ገልጸዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ላለው ስትራቴጅካዊ ግንኙነት ልዩ ቦታ እንደሚሰጥ የገለጹት ኮሚሽነሯ የኢትዮጵያ መንግስት ትብብሩን ለማጠናከር ያለውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ÷ኢትዮጵያ ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ ቁርጠኝነት እንዳላት ገልጸዋል፡፡

የአውሮፓ ሕብረት ለመልሶ ማቋቋምና መልሶ ግንባታ ስራዎች የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርግም አቶ ደመቀ ጥሪ አቅርበዋል።

Exit mobile version