Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሕዝቦቿ የተባበረ ብርቱ ጥረት ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ እናስረክባለን – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕዝቦቿ የተባበረ ብርቱ ጥረት ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ እናስረክባለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሁለተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ጆጎ ተፋሰስ በተካሄደው የማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የሁሉም ክልል ርዕሳነ መስተዳደሮችና የግብርና ቢሮ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ስላለው ተፅዕኖ በርካታ ዓለም አቀፍ ውይይቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም ተፅዕኖውን ለመቋቋም ወደ ተግባር በመግባት ረገድ ብዙ መጓዝ አለመቻሉን ጠቅሰው÷ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በማስጀመር ተፅዕኖውን ለመቋቋም ተምሳሌታዊ የተግባር እርምጃ ውስጥ መግባቷን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ እስካሁን በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ 32 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውንም ጠቅሰዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን በማንሳት፤ በሁለቱም ምዕራፎች የተተከሉ ችግኞች ብዛት 50 ቢሊየን ለማድረስ እቅድ መያዙን ነው የገለጹት።

ከአራት ዓመታት በፊት የጆጎ ተፋሰስ አካባቢ ምድረ በዳ እና ገላጣ ስፍራ እንደነበር ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትርሩ÷ አሁን ላይ አካባቢው በአረንጓዴ ተሸፍኗል ብለዋል።

ለዚህ ስኬት የአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ጠቅሰው÷ የአረንጓዴ ልማቱን መሰረት በማድረግም ማህበረሰቡ የንብ ማነብ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በአረንጓዴ ልማት የአፈር መሸርሸርን ማስቀረት፣ የዝናብ መጠንን መጨመርና ስርዓተ ምህዳረን ማስተካከል መቻሉን ገልጸው÷ ከዚህም ባለፈ ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ እየሆነ መጥቷል ነው ያሉት።

በቀጣይም የፍራፍሬ፣ የቡና፣ የሻይ እና ሌሎች ገበያ ተኮር የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላሳየው ብርቱ ጥረትና ላስመዘገበው ስኬት መንግስት ከፍተኛ ክብር እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በቀጣይም በአረንጓዴ አሻራ፣ በህዳሴ ግድብ፣ በስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን በሁሉም ዘርፍ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ስኬት አይቀሬነት የሚያረጋግጡ ውጤታማ ተግባራት በመንግስትና በህዝብ ትብብር እየተከናዎኑ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያን የለውጥ ጉዞ የማፅናትና ብልፅግናዋን የማረጋገጥ ጉዞን የሚያስቆም አንዳችም ምድራዊ ሃይል እንደማይኖር መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በሕዝቦቿ የተባበረ ብርቱ ጥረት ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ እናስረክባለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

Exit mobile version