Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ፕሬዚዳንት ኤርዶኻን በጠፈር ምርምር ዘርፍ ኤሎን መስክ ከቱርክ ጋር እንዲሰራ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ሀገራቸው በጠፈር ምርምር ዘርፍ የያዘችውን መርሐ-ግብር ኤሎን መስክ እንዲያግዝ ጠየቁ፡፡

ኤርዶኻን ከኤሎን መስክ ጋር ተገናኝተው የመከሩት በአሜሪካ ኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 78ኛው የተመድ ጠቅላላ የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን በነበራቸው ቆይታ መሆኑን አውት ሉክ ኢንዲያ አስነብቧል፡፡

ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን የአብረን እንሥራ ግብዣቸውን ለቢሊየነሩ ሲያቀርቡ “ስፔስ ኤክስ” በተባለው የጠፈር ምርምር ድርጅታቸው በኩል ጥያቄያቸውን እንደሚመልስ በመተማመን መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንሲ) እና በብሮድ ባንድ የሳተላይት ኢንተርኔት አገልግሎት ዘርፍም ቱርክ ከኤሎን መስክ ጋር በትብብር የመሥራት ፍላጎት አላት ተብሏል፡፡

በአብዛኞቹ አሜሪካውያን ዘንድ በተለይ በቴስላ ሞተርስ ኩባንያ በሚያመርታቸው የኤሌክትሪክ መኪኖቹ የሚታወቀው ኤሎን መስክ÷ በቱርክ 7ኛውን የኤሌክትሪክ መኪኖች ማምረቻ ኩባንያ የመክፈት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ኤሎን መስክ የድሮን ቴክኖሎጂ ላይ ከቱርክ ጋር በመተባበር መሥራት እንደሚፈልግ በሁለትዮሽ ውይይታቸው ወቅት የተሳተፉ የቱርክ የኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር መህመት ፋቲህ ካሲር ተናግረዋል፡፡

ኤሎን ሪቭ መስክ÷ በስፔስ ኤክስ፣ ቴስላ፣ ኤክስ ኮርፕ፣ ቦሪንግ፣ ኒውራ ሊንክ፣ ኦፕን ኤ አይ እና የሌሎች በርካታ ኩባንያዎች መሥራች፣ የተባባሪ መሥራች፣ የሊቀመንበር፣ የዋና ሥራ አሥፈፃሚ፣ የፕሬዚዳንትነት ወይም የምርት ሊቅነት የሥራ ድርሻ ያለው ሥራ ፈጣሪ ባለሀብት ነው፡፡

በአሁኑ ወቅትም ጠቅላላ የሐብት መጠኑ 226 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ይገመታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version