አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በምትዋሰንቸው ድንበሮች ተጨማሪ አምስት ኬላዎች በ1 ወር ውስጥ ልትከፍት ነው።
ኬላዎቹ የሚከፈቱት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ሲባል ቁጥጥሩን አመች ለማድረግ መሆኑን የኢምግሬሽን ዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አሳውቋል።
ኤጀንሲው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሳወቀው እንዲከፈቱ የተዘጋጁት 5 ኬላዎች በአፋር፣ሶማሌ ፣ አማራ ከልሎች እና በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ድንበር የሚገኙ ናቸው።
ከጎረቤት ሀገራት የሚያገናኙ 12 ኬላዎች የነበሩ ሲሆን ድንበሮቹ ሰፋፊ ከመሆናቸው አንፃር በህገወጥ መልኩ በእግራቸው አቋርጠው የሚገቡ ሰዎችን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ አድርጎት ነበር።
ይህን መነሻ በማድረግም ኮሮናን ለመከላከል የተቋቋመው እና በሰላም ሚኒስቴር የሚመራው ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣው ግብረ ሀይል በድንበር አካባቢ በሚገኙ ኬላዎች ላይ ጉብኝት አድርጓል።
በጉብኝቱ ያያቸወን ክፍተቶች መነሻ በማድረግም ተጨማሪ ኬላዎች እንዲከፈቱ በመወሰን በህገወጥ መልኩ ከጎረቤት ሀገራት የሚገቡ ሰዎችን ለመቆጣጠር እና ከህብረተሰቡ ጋር ሳይቀላቀሉ ወደ ለይቶ ማቆያ ለማስገባተ እንዲቻል ተጨማሪ አምስት ኬላዎች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ መወሰኑን ነው የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ተሬሳ የተናገሩት።
በነባሮቹ ኬላዎች ሲከናወን የነበረው ሙቀት የመለካት እና መሰል ተግባራት የሚከወኑ ሲሆን ወደ ለይቶ ማቆያ የመውሰድ ስራውም ይካሄዳል ተብሏል።
ከዚህ ቀደም በአፋር ከጅቡቲ በህገወጥ መልኩ ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ ሲሉ 22 ሰዎች መያዛቸውን የነገሩን አቶ ደሳለኝ ሰዎቹም ከህብረተሰቡ ጋር ሳይቀላቀሉ ተደርሶባቸው በሰመራ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ይገኛሉም ብለዋል።
ኮሚቴው ተጨማሪ ጥናት እንዲከናወንም አጥኝ ቡድን ወደ ድንበር አካባቢዎች ሊልክ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
አዲስ የሚከፈቱት ኬላዎች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ታምኖበታል።
ኬላዎቹ ሲከፈቱ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚያዋስኑ ድንበሮች 17 ኬላዎች ይኖሯታል።
በዙፋን ካሳሁን