የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል የኮሌራ መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀመረ

By Amele Demsew

September 16, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የኮሌራ መከላከያ ክትባት ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡

የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት÷ የኮሌራ በሽታ ጎንደር እና ባህር ዳርን ጨምሮ በክልሉ ባሉ 28 ወረዳዎች መከሰቱን አስታውቋል፡፡

ለጤና ባለሙያዎች በተሰጠው ስምሪት መሰረት የበሽታውን መስፋፋት መግታት ቢቻልም÷በበሽታው የተያዙ ሰዎች በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በመሄዳቸው በሽታው ወደሌሎች አካባቢዎችም ሊስፋፋ መቻሉ ተጠቅሷል።

ክትባቱ ጎንደር እና ባሕር ዳር ከተሞችን ጨምሮ በዘጠኝ ወረዳዎች ከአንድ ዓመት በላይ ለሆናቸው ሁሉ በተመረጡ ጤና ተቋማት መሰጠት መጀመሩን የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡