አዲስ አበባ ፣ መስከረም 5 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ኃይፐር ሶኒክ ሚሳኤሎቿን እና ኒውክሌር የመሸከም ዐቅም ያላቸው ቦንቦቿን ለሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን አስጎበኘች፡፡
ኪም ጆንግ ኡን ÷ በዛሬው ዕለት ከፓስፊኳ ከተማ ቭላደቮስቶክ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኔቪቺ ሲደርሱ በሩሲያው መከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ሾይጉ ደማቅ ወታደራዊ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
ሰርጌይ ሾይጉ ከኪም ጋር በነበራቸውም ቀጣይ መርሐ -ግብር ሀገራቸው “ኪንዝል” ብላ የምትጠራቸውን ኃይፐር ሶኒክ ሚሳኤሎች እና ኒውክሌር የመሸከም ዐቅም ያላቸውን ስትራቴጂክ ቦንቦች አስጎብኝተዋቸዋል፡፡
ኪም ጆንግ ኡን መሳሪያዎቹን በጥንቃቄ እንደተመለከቷቸው እና አድናቆታቸውን እንደቸሯቸው መገለጹንም ቲ አር ቲ ዘግቧል፡፡
ኪም በዛሬው ዕለት የጎበኙት ኔቪቺ የተሠኘው ማዕከል ÷ በሩሲያ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው እና ሀገሪቷ የጠፈር ፣ ወታደራዊ እና ሌሎች የቴክኖሎጂ መገልገያዎችን የምታበለፅግበት ነው ተብሏል፡፡