ቢዝነስ

የማምረቻ ሼዶች የተረከቡ ባለሐብቶች ወደ ሥራ እየገቡ ነው ተባለ

By Alemayehu Geremew

September 15, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማምረቻ ሼዶችን እና የለሙ መሬቶችን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር የውል ስምምነት ተፈራርመው የተረከቡ አምራች ኩባንያዎችና ባለሐብቶች ወደ ሥራ እየገቡ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የግንባታ ፣ የቅድመ ኦፕሬሽን እና የማሽን ገጠማ ሥራዎቻቸውን እያጠናቀቁ መሆኑን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ለአብነትም “ኢዘም ትሬድ ኤንድ ኢንቨስትመንት” ÷ ከ14 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ መዋዕለ-ንዋይ በማፍሰስ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ 3 ሺህ ሜትር ስኩዌር የማምረቻ ሼድ ተረክቦ ማምረቻ ማሽነሪዎቹን ገጣጥሞ እያጠናቀቀ መሆኑና በቅርቡም ሙሉ ለሙሉ ሥራ እንደሚጀምር ገልጿል፡፡

“ኒልኮን ኤሌክትሪክ ማኑፋክቸሪንግ” የተሰኘ ሌላ ኩባንያም እንዲሁ ከ11 ሚሊየን ዶላር በላይ በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና መዋዕለ-ንዋዩን በማፍሰስ 3 ሺህ ሜትር ስኩዌር የማምረቻ ሼድ መውሰዱንና ማሽነሪዎችን በማስመጣት መገጣጠም መጀመሩን አመላክቶ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባም ኮርፖሬሽኑ ጠቁሟል፡፡

ሁለቱ ኩባንያዎች በሙሉ አቅማቸው በቅርቡ ሥራ ሲጀምሩ ከ800 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ነው የተባለው።