አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የ2016 የመማር ማስተማር ስራን ማስጀመር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ምክትል ሃላፊ ኤፍሬም ተሰማ÷ በ2016 የትምህርት ዘመን ከ11 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት መድረጉን ተናግረዋል፡፡
የተመቸ የትምህርት ከባቢን ለመፍጠር በክረምቱ ከ2 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች እና ከ2 ሺህ በላይ የመምህራን መኖሪያ ቤቶች መታደሳቸውን አንስተዋል፡፡
የመምህራንን ብቃት ለማሳደግ በክልሉ ለሚገኙ 9 ሺህ የቅድመ መደበኛ መምህራን አጫጭር ስልጠና እንደሰጣቸው ጠቅሰው÷ ይህም የመምህራንን ቁጥር ወደ 32 ሺህ ከፍ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል፡፡
እስካሁን ከ9 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ተመዝግበዋል ያሉት ምክትል ሃላፊው÷ ቀሪዎቹ በቀጣይ ቀናት ይመዘገበሉ ብለዋል፡፡
ተማሪዎች እና መምህራንም ለመማር ማስተማ አስፈላጊውን ቁሳቁስ አሟልተው መዘጋጀታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መማሪያ መጽሐፍን ተደራሽ ለማድረግ 27 ሚሊየን መጽሐፍ ከውጭ መታዘዙን ጠቅሰው÷ በዚህ ወር 11 ሚሊየን መጽሐፍ ይሰራጫል ብለዋል፡፡
በክልሉ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ትምህርት መስከረም 7 ቀን የሚጀመር ሲሆን÷ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ደግሞ መስከረም 14 ቀን እንደሚጀምር ተጠቁሟል፡፡
በአልማዝ መኮንን