Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ሃይል የሚያመነጩ ተርባይኖችን ቁጥር 7 ለማድረስ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሃይል የሚያመነጩ ተርባይኖችን ቁጥር 7 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት÷በ2014 ዓ.ም ሃይል ማመንጨት ከጀመሩት ሁለት ተርባይኖች በተጨማሪ በያዝነው ዓመት 5 ተርባይኖችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው፡፡

5ቱ ተርባይኖች ወደ ስራ ሲገቡ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያላትን 4 ሺህ 818 ሜጋ ዋት የሃይል አቅርቦት መጠን ከፍ ያደርገዋልም ብለዋል ፡፡

ወደ ስራ ከገቡት ሁለት ተርባይኖች አንጻር ዘንድሮ ወደ ስራ የሚገቡት 5ቱ ተርባይኖች ሃይል መጠን የበለስ ፣የግልገል ጊቤ አንድና ሁለት እንዲሁም የተከዜ የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከሚሰጧቸው አማካይ 1 ሺህ 180 ሜጋ ዋት ተመጣጣኝ ወይም የሚበልጥ ሃይልን ያመነጫሉ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡

ይሁንና ከአቀማመጡና ከውሃ ፍሰቱ አኳያ የእነዚህን አምስቱ የሃይል ማመንጫ ተርባይኖች ሃይል የማመንጨት አቅም አሁን ላይ ይህን ያህል ነው ብሎ መናገር እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ በ13ቱ ተርባይኖች 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይልን ወደ ብሄራዊ የሃይል ቋት እንደሚቀላቀልም ነው ሚኒስተሩ የገለጹት፡፡

በዚህም÷ እያንዳንዳቸው ተርባይኖች በአማካይ ከ375 በላይ ሜጋ ዋት ሃይልን ያመነጫሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Exit mobile version