አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት በኳታር ዶሃ በሚካሄደው ዓለም ዓቀፍ ልዩ የቡና ትርኢት ላይ እየተሳተፈች ነው።
በኳታር የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ፈይሰል አልይ÷ የቡና ትርኢቱ አምራችና ገዢዎችን በቀጥታ ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ፣ ልዩ ጣዕምና ጥራት እንዲሁም ብዙ አይነት ቡናዋን ለዓለም በተለይም ለኳታር ህዝብ የምታስተዋውቃበት መድረክ እንደሆነም አስረድተዋል።
ይህም በኳታር የሚገኙ ቡና አስመጪ ኩባንያዎች ምርቶቻችንን አይተው በቀጥታ እንዲገዙም ሆነ ቀጣይ ግንኙነት ለመመስረት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ነው ያሉት አምባሳደር ፈይሰል።
በንግድ ትርዒቱ የተሳተፉት የቡና አምራች ኩባንያዎች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና የውጭ ምንዛሪ እንዲጨምር ይህንን የንግድ ትርዒት እንደ አንድ አማራጭ መጠቀማቸውን መጥቀሳቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ዓለም ዓቀፍ ልዩ የቡና ትርኢት ቡና በማቀነባበር፣ በማልማት፣ በማምረት፣ በመሸጥና ተያያዥ ዘርፎች የተሰማሩ የተለያዩ ሀገራት የንግድ ድርጅቶች እየተሳተፉ ነው፡፡