አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቴክኒክ ባለሙያዎች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ጋር በመሆን መስቀል አደባባይ እና ጃን ሜዳን በሚመለከት ምክክር አድረጉ።
ምክክራቸውን አጠናቀው ፕሮጀክቶቹን በተመለከተ ከስምምነት ላይ በመድረስ የጋራ ግብረ ኃይል ማቋቋማቸውን አስታውቀዋል።
የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክትን የጋራ ጥምር ኮሚቴው የጎበኘ ሲሆን፥ የአፈር ቁፋሮው 70 በመቶ ያህል መጠናቀቁ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሊቀስዩማን እስክንድር ገብረክርስቶስ፥ ፕሮጀክቱ በሶስት ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅ እና በመስቀል በዓል ላይ ተጽዕኖ እንደማይፈጥር ከስምምነት ላይ ደርሰናል ብለዋል።
በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያኗ የቴክኒክ ባለሙያዎች የተካተቱበት ግብረ ኃይል አደባባዩን ለመስከረም ዝግጁ ከማድረግ ባለፈ ከተቋራጩ የዲዛይን ቡድን ጋር በጋራ በመሆን ተግባቦት እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በጊዜያዊነት የቀድሞውን አትክልት ተራ በመተካት ለመገበያያ ስፍራነት እያገለገለ በሚገኘው ጃን ሜዳ ጉዳይ ላይ መምከራቸውንና በተመሳሳይ በበዓለ ጥምቀት ላይ ክፍተት እንደማይፈጥር መግባባት መደረሱን ጠቅሰዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ የከተማ አስተዳደሩን ውሳኔዎች ቀድማ አለማወቋ ክፍተት ፈጥሮ መቆየቱን አምነው፥ በነበራቸው ምክክር ከዚህ በኋላ በቅርበት ለመስራት ተግባቦት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።
በአክሱም ገብረህይዎት