Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በህንድ የኒፓህ ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 3 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በህንድ ኬራላ ግዛት ኒፓህ በተባለ ቫይረስ 2 ሰዎች ለህልፈት መዳረጉን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲገደቡ ውሳኔ ተላለፈ።

ምንም አይነት ክትባት የሌለው ኒፓህ ቫይረስ ከፍተኛ ትኩሳትና የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን በመፍጠር የአንጎል እብጠት በማስከተል ለሞት እንደሚዳርግ ተጠቁሟል።

በመሆኑም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ህንድ ህዝብ በብዛት እንዳይሰበሰብ ገደብ የጣለች ሲሆን በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ኬራላ ግዛት አንዳንድ ትምህርት ቤቶችን እንዲዘጉ መደረጉን ቲአርቲ ዘግቧል፡፡

ኒፓህ ቫይረስ ከ40 እስከ 75 በመቶ ሞት እንደሚያስከትል የአለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

በቫይረሱ ከሞቱት ሁለት ሰዎች በተጨማሪ ሶስት ሰዎች በምርመራ ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል።

153 የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ በቫይረሱ ህይወታቸውን ካጡና ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው 700 ሰዎች የቅርብ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ ተገልጿል።

ቫይረሱ መነሻው ከሌሊት ወፍ እና ከአሳማ ተነስቶ ወደሰዎች የተዛመተ እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን ከሰው ወደ ሰው የሚዛመት እንደሆነም ተነግሯል።

የዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ስጋት ያላቸው ብሎ ከለያቸው ቫይረሶች መካከል አንዱ የሆነው ኒፓህ ቫይረስ በፈረንጆቹ 1998 በማሌዢያ ተከስቶ ጉዳት ማስከተሉን ዘገባው አስታውሷል።

Exit mobile version