Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አፕል አይፎን 15 የተሠኘውን አዲስ ተንቀሳቃሽ ሥልክ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አፕል ‘አይፎን 15’ የተሠኘውን አዲስ ተንቀሳቃሽ ሥልክ ለተጠቃሚዎቹ ይፋ አደረገ፡፡

ኩባንያው አዲሱን የተንቀሳቃሽ ሥልክ ምርቶቹን አይፎን 15 እና አይፎን 15 ፕላስ ጨምሮ ኤይር ፖዶቹን አሜሪካ ካሊፎርኒያ በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ኩፔርቲኖ ለደንበኞቹ ለዕይታ አቅርቧል፡፡

አዲሶቹ ምርቶች ከፈረንጆቹ መስከረም 22 ጀምሮ ገበያ ላይ ይውላሉ ተብሏል፡፡

ምርቶቹን እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደንበኞቹ በቀዳሚ የበዓላት ወቅት ሸመታቸው ዝርዝር ውስጥ አካተውታል፡፡

እንደ ቀዳሚዎቹ ምርቶቹ ሁሉ አፕል አይፎን 15 እና አይፎን 15 ፕላስ የሥልክ ቀፎዎቹን ሲያመርት የ6 ነጥብ 1 ኢንች የሥክሪን ልኬት መጠን እና የ6 ነጥብ 7 ኢንች የሥክሪን ልኬት መጠን እንደየ ቅደም ተከተላቸው ተጠቅሟል፡፡

ሁለቱም አዳዲስ ሞዴል ተንቀሳቃሽ ሥልኮች 48 -ሜጋ ፒክስል “ዋና ካሜራ” ሲኖራቸው የፕሮ ማክስ ካሜራ ምሥል የማጉላት ዐቅም እስከ 5 እጥፍ መሆኑን እና በርቀት ላይ ያለ ምስልን የማቅረብ ዐቅም ደግሞ 3 እጥፍ መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

አዲሶቹ የአፕል ተንቀሳቃሽ ሥልኮች ÷ በቀጣይ ኩባንያው ለገበያ ሊያቀርብ ያሰበውን “ቪዥን ፕሮ” የተሰኘ የጆሮ ማዳመጫ ይፋ ሲያደርግ ተጠቃሚዎቹ በጆሮ ማዳመጫው ሊያዩዋቸው የሚችሏቸውን ተንቀሳቃሽ ምሥሎች መቅዳት እንዲችሉ ታስቦ ነው የተሠሩት።

አይፎን 15 ፕሮ 999 ዶላር እንዲሁም አይፎን 15 ፕሮ ማክስ 1 ሺህ 199 ዶላር የመሸጫ ዋጋ ተቆርጦላቸዋል፡፡

ለተንቀሳቃሽ ሥልኮቹ ጠርዞችም እንደ በፊቱ የማይዝግ ብረት (ስቴይንለስ እስቲል) ከመጠቀም ይልቅ “ቲታኒየም” የተሰኘውን ማዕድን ተጠቅሞ መፈብረክ እና ተጠቃሚዎቹን መድረስ መርጧል፡፡

እንደ ሲ.ኤን.ቢ.ሲ.ዘገባ ደግሞ ÷ አይፎን 15ን መጀመሪያ ሲመለከቱት ከቀደመው ሞዴል ምንም ልዩነት የለውም ብለው ሊገረሙ ይችላሉ ፤ ነገር ግን ሲይዙት እጅዎ ላይ ቀልል ማለቱን ይረዳሉ፡፡

ይህ የሆነው አፕል ለሥልኮቹ ጠርዞች “ቲታኒየም” በመጠቀሙ ክብደቱ በተጨባጭ መቀነሱን እና ኪስ ላይም ቅልል ማለቱን ሲረዱ ደግሞ ይደነቃሉ ብሏል፡፡

በአዲሶቹ የአይፎን እና የኤርፖድ ፕሮ ምርቶቹ ቀደም ሲል ይጠቀምበት የነበረውን የኃይል ማስተላለፊያ ገመድ ትቶ በአውሮፓ ኅግ መሠረት ወደ “ዩ.ኤስ.ቢ-ሲ” የልኬት መጠን ቀይሯል።

የ“ዩ.ኤስ.ቢ-ሲ” የልኬት መጠን ለባለሙያዎች ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያለውን ተንቀሳቃሽ ምሥል ከአዲሶቹ አይፎን ምርቶች በቀጥታ ወደ ተለያዩ ቁሶቻቸው ለማስተላለፍ ቀላል ያደርግላቸዋልም ተብሏል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version