አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ኮርያ መንግሥት ከሀገሪቱ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚውሉ የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገች።
ድጋፉ 28 ሺህ 33 የመመርመሪያ ኪቶች፣ 150 ሺህ 400 የፊት ጭንብል፣ 60 ሺህ ዶላር የሚያወጣ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘሮችን ያጠቃልላል።
ጎን ለጎንም ለኮሮናቫይረስ መከላከል የሚውል ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፥ ድጋፉ በአገር አቀፍ ደረጃ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ሥራ ያጠናክራል ብለዋል።
የኮርያ መንግሥት በኮሮና ቫይረስ መከላከል ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የጤና ዘርፍ ሥራዎች ላይ አጋር መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሁን ሚን ሊም እንደተናገሩት፤ የኮርያ መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ከኢትዮጵያ ጋር ይተባበራል።
ኮርያ በዓለም ደረጃ አሳሳቢ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የምታከናውናቸውን በጎ ተግባራትና ልምድ ለኢትዮጵያ ታካፍላለች ብለዋል።
በዚህ ላይ ያለውን አጋርነት በተለይም በኢንተርኔት በመታገዝ እንደምታጠናክር ገልጸው፤ በቀጣይም ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ድጋፍ በሚያስፈልጋት ሁሉ ኮርያ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አምባሳደሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።