Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አምራቹን ዜጋ በቴክኒክ፣ በሃሳብና በግብዓት መደገፍ ይገባል – አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አምራቹን ዜጋ በቴክኒክ፣ በሃሳብና በግብዓት መደገፍ ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

በክልሉ “ከሸማችነት ወደ አምራችነት” በሚል መሪ ሃሳብ የአምራችነት ቀን በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተከብሯል።

ቀኑ አምራች ተቋማትና ዜጎች የሚታወሱበት፣ እያበረከቱ ያለዉ አስተዋጽኦ ዕውቅና የሚሰጥበትና ለላቀ አምራችነት የሚነሣሡበት እንደሆነ ተመላክቷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ ያለውን የግብርና አሰራር ዘይቤን ስር ነቀል በሆነ መንገድ መቀየር ያስፈልጋል።

አምራቹን ዜጋም በቴክኒክ፣ በሃሳብና በግብዓት ሊደገፍ እንደሚገባ ገልጸው፤ ሁሉም ባለድርሻና ተባባሪ አካላት ከወትሮው በተሻለ መልኩ ተደጋግፎና ተባብሮ በትኩረት መስራት እንደሚገባው አስረድተዋል።

አዲሱን 2016 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በብሩህ ተስፋ ለመቀበል የጳጉሜን ቀናት ስናከብር በወንድማማችነት እሴት ላይ የቆየ ህብረ ብሔራዊ አንድነት በማጠናከር ሊሆን ይገባል ማለታቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መረጃ ጠቁሟል።

በክረምት ወራት የየተጀመሩ ሰው ተኮር ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቡን ዊው በበኩላቸው ምርታማነትን በሚጨምሩና ልማትን በሚያረጋግጡ የግብርናና ሌሎች ምርቶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

Exit mobile version