አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለት ሴት ኢትዮጵያውያን በአሜሪካው ታይም መፅሔት የፈረንጆቹ 2023 ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።
በታዋቂው መፅሔት ዓለም ላይ በተፅዕኖ ፈጣሪነት የተካተቱት ኢትዮጵያዊቷ ተመራማሪ አበባ ብርሃኔ እና ትምኒት ገብሩ (ዶ/ር) ናቸው።
ሁለቱ ኢትዮጵያውያን በአሰላሳይ ዘርፍ በተያዘው የፈረንጆቹ አመት ዓለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ግለሰቦች መካከል መካተታቸውን መፅሔቱ ይፋ አድርጓል።
አበባ ብርሃኑ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) የመረጃ ሰርዓት መመዘኛ ሞዴል ያስተዋወቀች ሲሆን፥ በአየርላንድ በሚገኘው የሞዚላ ፋውንዴሽን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ከፍተኛ አማካሪ እና በደብሊን ኮሌጅ በረዳት ፕሮፌሰርነት ታገለግላለች።
ተመራማሪዋ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የመረጃ አወሳሰድ እና ማበልፀጊያ ውስጥ የሚገኙ መረጃዎች ከወገንተኝነት ነፃ እንዲሁኑ የሚያስችል ምርምር ይፋ ማድረጓም ነው የተገለጸው።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚበለፅገው ከትላልቅ የመረጃ ስብስቦች፣ ከኢንተርኔት እና ከምስል ስብስቦች ከተወሰደ መረጃ መሆኑንም ተመራማሪዋ ገልጻለች፡፡
ይህም ግለሰቦች የግል ፍላጎታቸውን በሰው ሰራሽ አስተውሎቶች ስልታዊ በሆነ መንገድ ሊያስተላልፉበት እንደሚችሉ በመጥቀስ፥ በዚህም በሰው ሰራሽ አስተውሎቶች ዘረኝነት፣ የፆታ መድልኦ እና ወገንተኝነት ሊስተዋልባቸው እንደሚችል አስረድታለች፡፡
ይፋ ያደረገችው የሰው ሰራሽ አስተውሎት መረጃ መመዘኛ ሞዴል መረጃዎቹ ሚዛናዊነትን ያገናዘቡ መሆናቸውን ይተነትናል ተብሏል፡፡
ሞዴሉ አስተማማኝ እና ዘላቂ አይደለም የምትለው አበባ ያዘጋጀችው ሞዴል ዋጋ ውድ በመሆኑ ዝቅተኛ የእድገት አቅም ባላቸው ሀገራት ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን ገልፃለች፡፡
በኮምፒውተር ተማራመሪነት የምትሰራው ትምኒት ገብሩ (ዶ/ር) የዓመቱ 100 ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ውስጥ አንዷ ሆና ተካታለች።
በተመሳሳይ መልኩ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ምርምር እና ጥናት የምትሰራው ትምኒት በጎግል ኩባንያ በከፍተኛ የሃላፊነት ቦታ ላይ መስራቷ የሚታወስ ነው።
ከጎግል ኩባንያ ጋር ከተለያየች በኋላ ለጥቁሮች እና ሴቶች ፍትሐዊ ቴክኖሎጂ የሚታገል የሰው ሰራሽ ልኅቀት የምርምር ተቋም መስርታ እየሰራች ሲሆን፥ ይህ ስራዋም እውቅናን አስገኝቶላታል።
ትምኒት ከዚህ ቀደም በታዋቂዎቹ ፎርቹን እና ፎርብስ መፅሄቶች ከዓለማችን በሳይንስ እና በቴክሎጂ ዘርፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸው ካላቸው ሴቶች መካከል አንዷ ናት።