የሀገር ውስጥ ዜና

ከ30 ቢሊየን ብር በላይ የታክስ ጉዳት አድርሷል የተባለው ተከሳሽ ማረሚያ ቤት እንዲወርድ ታዘዘ

By Amele Demsew

September 08, 2023

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ30 ቢሊየን ብር በላይ የታክስ ጉዳት በመንግስት ላይ አድርሷል የተባለው ተከሳሽ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጎ ማረሚያ ቤት እንዲወርድ ታዘዘ፡፡

ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ወንጀል ተረኛ ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሹ በረከት አለልኝ በአ/አ ከተማ በለሚኩራ ክ/ከ ወረዳ 9 በተለምዶ አትሌቶች ሰፈር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ኗሪ ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳሪክቶሬት ዐቃቢህግ በተከሳሹ ላይ ተደራራቢ ክሶችን ማቅረቡ ይታወሳል።

ተከሳሹ ‘ሰለሞን ሙሉ ከዉን’ በሚል ሀሰተኛ ማንነት የኗሪነት መታወቂያ አዘጋጅቶ መጠቀም፣ ሀሰተኛ ንግድ ፍቃድ በማውጣት፣ ሀሰተኛ የግብር ሰነዶችን በመጠቀምና በመስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ከጁፒተር ንግድ ስራዎች ድርጅት በመረከብ ደረሰኞችን እያተመ ለተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ሲያሰራጭ እንደነበር ዐቃቤ ህግ ጠቅሶ ነበር።

ተከሳሹ ያተመውን ደረሰኝ በማሰራጨት የንግድ ትርፍና የተጨማሪ እሴት ታክስ ማለትም ባጠቃላይ 13 ቢሊየን 147 ሚሊየን 368 ሺህ 295 ብር ጉዳት ያደረሰ መሆኑም በክሱ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም÷ ተከሳሹ ለ339 ግብር ከፋዮች 1 ሺህ 663 ደረሰኞችን በማሰራጨት በ15 የገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች 25 ቢሊየን 989 ሚሊየን 943 ሺህ 223 ብር የግብአት ታክስ ተመላሽ እና በንግድ ትርፍ ወጪነት የቀረበ በመሆኑ ተመሳሳይ መጠን ያለው ጉዳት አድርሷል በማለት ዐቃቤ ህግ በክሱ ላይ ዘርዝሯል።

ባጠቃላይ ተከሳሹ በፈጸመው የወንጀል ተግባር ከ30 ቢሊየን ብር በላይ የታክስ ጉዳት በመንግስት ላይ አድርሷል ተብሎ በዝርዝር ክሱ ላይ ተገልጿል።

ተከሳሹም ክሱ ከደረሰው በኋላ በጠበቆቹ በኩል የዋስትና መብቱ እንዲከበርለት ለተረኛ ችሎቱ ጥያቄ አቀርቧል።

በከሳሽ ዐቃቤ ህግ በኩል ደግሞ የቀረበው ክስ ተደራራቢ በመሆኑና በመንግስት ላይ የደረሰው ጉዳት መጠን ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቀረበበት የሙስና አዋጅ ድንጋጌ ከ10 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ መሆኑ ተጠቅሶ የዋስትና መቃወሚያ ቀርቦ ክርክር ተደርጓል።

ክርክሩን የመረመረው ተረኛ ወንጀል ችሎቱ በተከሳሹ ላይ በቀረበው አንደኛው ክስ ከ5 ዓመት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ እስራት የሚያስቀጣ ድንጋጌ መሆኑ ተጠቅሶ የቀረበው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርድ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

ተከሳሹ የክስ መቃወሚያ ካለው ለመጠባበቅ ለጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ