የሀገር ውስጥ ዜና

የሀገር አንድነትና ሉአላዊነት የሚፀናው ሁሉም በተሰማራበት መስክ በሚከፍለው መስዋዕትነት ነው – አቶ ኦርዲን በድሪ

By Amele Demsew

September 07, 2023

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር አንድነትና ሉአላዊነት የሚፀናው ሁሉም በተሰማራበት መስክ በሚከፍለው መስዋዕትነት ነው ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

በሐረሪ ክልል ጳጉሜን 2 የመስዋዕትነት ቀን “በመስዋዕትነት የምትፀና ሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ ተከበሯል፡፡

በዕለቱ ለሃገር ሉዓላዊነት መከበር የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ለከፈሉ የመከላከያ፣ ለፌደራልና ለክልሉ ፖሊስ ሠራዊት አባላት እንዲሁም ለማረሚያ ፖሊስና ለሚሊሺያ አባላት ክብርና ምስጋና ቀርቧል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ኦርዲን በድሪ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ በልጆቿ መስዋዕነት በቅኝ ያልተገዛች የአሸናፊዎች ሀገር የነፃነት ቀንዲል ሆና ታፍራና ተከብራ ለትውልድ ተሸጋግራለች።

ኢትዮጵያ በማይናወጥ አለት ላይ የተመሰረተች ሀገር በመሆኗ የሀገር አንድነትና ሉአላዊነት የሚፀናው ሁሉም በተሰማራበት መስክ በሚከፍለው መስዋዕትነት በመሆኑ በትጋት መሰራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

የክልሉ የሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን ዋደራ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር የተሰዉ ጀግኖች ሲዘከሩና ሲታወሱ እንደሚኖሩ ገልፀዋል።

ዛሬም በቆራጥ ልጇቿ ሠላምና ብልፅግናዋም ለማረጋገጥ መስዋዕትነት እየተከፈለ መሆኑን ገልጸዋል።

በዕለቱ ለሀገር ሠላምና ሉዓላዊነት መረጋገጥ ለተሰዉ ጀግኖች ቤተሰቦችና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው የፀጥታ አካላት እውቅናና ሽልማት የተሰጠ ሲሆን የህይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ ቤተሰቦች ደግሞ የበዓል መዋያ የፍጆታ እቃዎች ተበርክቷል።

በተሾመ ኃይሉ