አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) አምባሳደር መስፍን ገብረማርያም የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሩዋንዳ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ አቅርበዋል።
በዚህ ወቅት የሩዋንዳ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በሩዋንዳና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ልዩና ታሪካዊ እንዲሁም ወንድማዊ መሆኑን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ በሩዋንዳ የሚኖራቸው ቆይታ የተሳካ እንዲሆንም መንግስታቸው ሁሉንም ዓይነት ድጋፍ እንደሚያደርግም ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል።
አምባሳደር መስፍን ገብረማርያም በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያና በሩዋንዳ መካከል ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረውን ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩም ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያም ከሩዋንዳ ጋር ታሪካዊና ወንድማዊ ግንኙነት እንዳላት እንደምታምንና በዚህም መንፈስ ሁሉንም ተግባራት እንደምታከናውን ጠቁመዋል።
አምባሳደር መስፍን የሹመት ደብዳቤያቸውን ካቀረቡ በኋላ ከሩዋንዳ የሚዲያ ተቋማት ጋር በነበራቸው ቆይታም ሁለቱ ሀገራት የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸውም ነው የተናገሩት፡፡
በተለይም በ1994 በሩዋንዳ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ በመላክ ለሩዋንዳ መረጋጋት አስተዋጽኦ ማድረጓን አስታውሰዋል።
ሀገራቱ የነበራቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም በርካታ ስምምነቶች መፈራረማቸውንም ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት በቀጣይ 3ኛውን የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚቴ ስብሰባ ማካሄድ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ እንደሚሰሩ አምባሳደሩ መግለጻቸው ኢዜአ ዘግቧል።