Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በመዲናዋ ለዘመን መለወጫ በዓል በቂ የመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት መኖሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ለመጪው አዲስ ዓመት በዓል የመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር እየተሠራ መሆኑን የከተማዋ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሰውነት አየለ እንዳሉት÷ ለበዓሉ የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በብዛት እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

በከተማዋ በሚገኙ 25 ቦታዎች ባዛር መዘጋጀቱን ጠቁመው÷ በዚህም ለበዓል የሚውሉ አሥፈላጊ ግብዓቶች እየቀረቡ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በከተማዋ በሚገኙ 172 የእሑድ ገበያዎች ልዩ ዝግጅት ተደርጎ አስፈላጊ የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ይህም አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት በህገ-ወጥ ደላላዎች ሰንሰለት ሊፈጠር የሚችልን የዋጋ ንረት እንደሚያስቀር አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል በ152 ሸማት ማኅበራት እና በሠባት ትላልቅ ገበያዎች የበዓል ፍጆታ ዕቃዎች ለገበያ መቅረባቸውን ነው የገለጹት፡፡

በዚህ መሠረትም ፥ ከ1 ነጥብ 25 ሚሊየን ሊትር በላይ ዘይት፣ 52 ሺህ ኩንታል ጤፍ፣ 30 ሺህ ኩንታል የስንዴ ዱቄት፣ ከ36 ሺህ ኩንታል በላይ ቀይ ሽንኩር እና ሌሎች ግብዓቶች ለሸማቾች መቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡

ከእንስሳት ተዋጽዖ ጋር በተያያዘም 7 ሺህ የሚደርሱ የቀንድ ከብቶች፣ በርካታ በጎች እና ፍየሎች እንዲሁም 3 ሚሊየን እንቁላል ለገበያ ቀርቧል ነው ያሉት፡፡

በገበያ ላይ የሚስተዋሉ ህገ- ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከልም ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በበዓል ወቅት ምርት የመደበቅ፣ ባዕድ ነገር መቀላቀል፣ ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶችን የመሸጥና የተለያዩ የገበያ አሻጥሮችን በሚፈጥሩ ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድም አስገንዝበዋል፡፡

ማኅበረሰቡም ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ሲመለከት በአቅራቢያ ለሚገኙ የጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version