የሀገር ውስጥ ዜና

የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

By Amele Demsew

September 02, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳለፈ፡፡

በዚሁ መሠረት በክልሉ የጳጉሜ ቀናት የአብሮነት እሴቶችን በሚያሳድጉ፣ የአገልጋይነት ባህልና እሴትን በሚያጎለብቱና ኅብረ ብሔራዊ እሴቶችን በሚያጸኑ የተለያዩ ክንውኖች እንደሚከበር ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

26ኛው ዓለም አቀፍ የሐረሪዎች ስፖርት እና የባህል ፌስቲቫል በሐረር ከተማ እንዲከበር መወሰኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

ፌስቲቫሉ በተለየዩ ሀገራት የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች እና የሐረሪ ወዳጆች ገንዘባቸውንና እውቀታቸውን ለክልሉ ልማት እንዲያውሉ የሚያስችል መድረክ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም የፌስቲቫሉ በክልሉ መከበር የሐረሪን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትና የቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚን ለማጎልበት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ነው የተባለው።