የሀገር ውስጥ ዜና

የመሰረታዊ ፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

By Amele Demsew

September 01, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የመጪው ዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የመሰረታዊ ምርቶች አቅርቦት እጥረትና ዋጋ ንረት እንዳይኖር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በልሁ በሰጡት መግለጫ÷ የፍላጎትና አቅርቦት ያለመመጣጠን፣ የሸቀጦች ዝውውር በኬላ መገደብ፣ የጸጥታ ችግርና የአለም ዋጋ መጨመር ለዋጋ መናር ምክንያ ናቸው ብለዋል፡፡

መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል ተከትሎም በመስከረም ወር በዓላት ስለሚበዙ በሸማቹ ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ከክልሎችና ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በቅዳሜና እሁድ ገበያ በኩል ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ የግብርና፣ የኢንዱስሪና አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽን ምክትል ስራ አስፈጻሚ ቀጸላ ሸዋረጋ በበኩላቸው÷ ኮርፖሬሽኑ ለበዓሉ 11 ሚሊየን ሊትር ፓልም ዘይት ለክሎችና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ግብዓቶች አቅራቢ ድርጅት በኩል ደግሞ ከ16 ሚሊየን ሊትር በላይ ዘይት ቀርቧል ነው ያሉት፡፡

በበዓሉ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ተገልጿል፡፡