ቢዝነስ

ተገበያዮች ባሉበት ሆነው የሚገበያዩበት መተግበሪያ ወደ ስራ ሊገባ ነው

By Melaku Gedif

September 01, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተገበያዮች ባሉበት ቦታ ሆነው ግብይት የሚፈጽሙበት መተግበሪያ በ2016 ዓ.ም ወደ ስራ ሊያስገባ መሆኑ ተገለጸ።

መተግበሪያው አቅራቢውና ላኪው ካሉበት ቦታ ሆነው በቀላሉ ግብይት መፈፀም የሚችሉበት መሆኑ ተመላክቷል።

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስተባባሪነት በመንደፍ በአርቴፍሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት አማካኝነት የበለጸገው መተግበሪያው በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ስራ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

ምርት ገበያው ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት በመተግበር ጥራትን መሠረት ያደረገ ግልጽና ተወዳዳሪ ሥርዓት ገንብቶ ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶች በጥራት እያገበያየ እንደሆነ ተገልጿል።

ምርት ገበያው በተቋማዊ ሪፎርም ከሚተገብራቸው ስራዎች አንዱ የሆነው የበይነ መረብ ግብይት (Online Trade) ተገበያዮች ባሉበት ቦታ ሆነው መገበያየት የሚችሉበት ዕድል መፍጠር እንደሆነ ተነግሯል።

በተጨማሪ ተገበያዮች ያለማንም ጣልቃገብነት የግብይት ትዕዛዞቻቸውን ማስገባትና ወደ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መ/ቤት ወይም የቅርንጫፍ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላት ሳይመጡ ማረጋገጥና ማየት የሚፈልጓቸውን መረጃዎች መመልከት እንደሚያስችላቸው ተጠቁሟል።

ተገበያዮች ከዚህ በፊት አገልግሎቶችን ለማግኘት የግድ ምርት ገበያ መምጣት ይጠበቅባቸው እንደነበር የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መረጃ አመልክቷል።

መተግበሪያው ወደ ስራ ሲገባ ተገበያዮች በቅድመ ግብይት ወቅት ማሟላት ያለባቸውንና ተያያዥ አገልግሎቶችን ኹሉ ባሉበት ቦታ ኾነው ማሳካት እንደሚችሉም ገልጿል።