ዓለምአቀፋዊ ዜና

በኒጀር በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት 20 ሰዎች ተገደሉ

By Tibebu Kebede

May 11, 2020

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኒጀር በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት 20 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን የሃገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።

ጥቃቱ ቲላበሪ በተባለው ግዛት በሚገኙ የተለያዩ መንደሮች የተፈጸመ መሆኑንም ነው ባለስልጣናቱ ያስታወቁት።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱትና ከአሸባው አልቃይዳ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉት ቡድኖች ጥቃቱን ሳይፈጽሙት አልቀረም ነው የተባለው።

ኒጀር ከማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ቤኒን ድንበር የምትዋሰንበት ይህ አካባቢ በታጣቂዎች በተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚፈጸምበት ይነገራል።

በተለይም ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ ሰርጎ ገብ ታጣቂዎች በአካባቢው ባደረሱት ጥቃት በርካቶች ለህልፈት ተዳርገዋል።

ካለፈው አመት ታህሳስ ወር ወዲህ በፈጸሙት ጥቃትም 170 የመንግስት ወታደሮች ተገድለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም ታጣቂዎች የኮሮና ቫይረስን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሳህል ቀጠና የሚፈጽሙትን ጥቃት ሊያጠናክሩ ይችላሉ በሚል ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

ጥቃቱ የተፈጸመበት ግዛት ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ይገኛል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።